በአሶሳ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተመራ ልኡክ ከአዲስ ቻምበር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር የጋራ ውይይትና የልምድ ልውውጥ አካሄደ

ከተመሰረተ ሶስት አስርት አመታትን ሊደፍን ጥቂት የቀረው የአሶሳ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ሶስት ሺህ አባላትን በመያዝ የከተማውን ብሎም የክልሉን ንግድና ኢንቨስትመንት ለመደገፍ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ የዚህ ምክር ቤት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በአዲስ ቻምበር ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት ከምክር ቤቱ ኃላፊዎች ጋር የጋራ የውይይትና የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡ አዲስ ቻምበር የረጀም አመት ልምድና እውቀትን ያካበተ ንግድ ምክር ቤት በመሆኑ ለሌሎች በሀገሪቱ ለሚገኙ ንግድ ምክር ቤቶች የእውቀት ኀብት በመሆኑ ከምክር ቤቱ የሚያገኙት ዘርፈ ብዙ ልምድና ተሞክሮ በሂደት የአሶሳ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ሊያጠናክር እንደሚችል የልኡካን ቡድኑ አባላት ተናግረዋል፡፡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጥሮ ሀብት የታደለ እንደመሆኑ መጠን የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ባለ ሀብቶች ሙዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ማድረግ የአሶሳ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ሚና ብቻ ሳይሆን የአዲስ ቻምበርም ሚና መሆን እንዳለበት ልኡካኑ ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ ከምክር ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተሰጠ ሲሆን ምክር ቤቱ ያለውን ልምድና እውቀት እንዲሁም የቢዝነስ ተሞክሮን ለሌሎች መሰል ተቋማት በማካፈል ላይ እንደሚገኝ እና በኢትዮጵያ ጠንካራና ተወዳዳሪ የግል ዘርፍ እንዲፈጠር አላማ እንዳለው ተገለጿል፡፡ በመጨረሻም በመረጃ ላይ የተመሰረተ የአድቮኬሴ ስራዎችን መስራት፤ አጋርነት ማጠናከር እንዲሁም ጥራት ያለው አገልግሎትን በመስጠት ንግድ ምክር ቤቶች ተወዳዳሪና የቆሙለትን አላማ ሊያሳኩ እንደሚችሉ ከአዲስ ቻምበር ኃላፊዎች ምክር ሀሳብ ተለግሷል፡፡

wpChatIcon
wpChatIcon