ምክር ቤቱ በውል ግብርና (Contract Farming) ምንነት እና ጠቀሜታ ዙርያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄደ::

የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የግብርና ምርትን በተለይ ፍራፍሬ እና አታክልት አምራቾች እና አቀነባባሪዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በውል ግብርና አሰራር እና ጠቀሜታ ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የግብርና ምርቶችን በመጠቀም በማቀነባር ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ተወካዮች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል ፡፡
የውል ግብርና በሃገራችን ቀደም የነበረ እና በዘመናዊ መልክ አለመከናወኑ አዲስ እንደሚያስመስለው የተናገሩት እና የውል ግብርና በሌሎች ሃገሮች እና በሃገራችን ያለውን ተሞክሮ ያቀረቡት በማማከር ዘርፍ የተሰማሩት ደ/ር በየነ ታደሰ የውል ግብርና በከፍተኛ ሁኔታ በሌሎች ሃገሮች የሚሰራበት እና ውጤታማ የሆነ አፈጻጸሙ የተለያዩ ሂደቶችን የሚያካትት መሆኑን አንስተዋል::
እንደባለሞያው በሃገራችን የውል ግብርና ተግባራዊ የሆነባቸው ዘርፎች መኖራቸውንም አንስተዋል ::
በስኳር ፋብሪካዎች ፣በማር፣በገብስ እና በአቦካዶ ምርቶች ላይ ገበሬዎች ከአቀናባሪዎች ጋር በገቡት ውል የሚሰራባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የውል ግብርና አሁን ላይ ግንዛቤውን በመጨመር፡የህግ ማእቀፍ በማዘጋጀት እና የመንግስት አመራር ታክሎበት ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር መተግበሩ ጥያቄ ውስጥ መግባት የሌለበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የውል ግብርና የገበያ ትስስር መፍጠር የሚያስችል፡በገበያ ማፈላለግ ሂደት የሚወጡ ወጭዎችን መቀነስ የሚያስችል፡በአነስተኛ ደረጃ ያሉ ገበሬዎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርግ፡ ልምድ እና የእውቀት ሽግግር የሚፈጠርበት እንደሆነ ተብራርቷል፡፡
የውል ግብርና ክንውንን በሃገራችን ያለውን የፖሊሲ እንዲሁም ተግዳሮቶቹን እስመልክቶ ማብራርያ የሰጡት በግብርና ሚኒስቴር የውል ግብርና ቡድን መሪ አቶ ሱልጣን መሃመድ የውል ግብርና በምርት ሂደት የሚገጥሙ፡ጥራትን፡መጠንን እና ከምርት አይነት ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሄ መስጠት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል::
የውል ግብርና በሃገራችን በአዋጅ የተደገፈ እና በሌሎች ሃገሮች ተግባር ላይ የሚውሉ አሰራሮችን የሚከተል ነውም ብለዋል::
ባሳለፍነው 2014/15 ዓ.ም 772,857 ሄክታር መሬት በዚሁ በውል ግብርና አገልግሎት ላይ የዋለ ሲሆን፡በዚህም16,883,304 ኩንታል የምርት አይነት መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *