ለሴት ሥራ ፈጣሪዎችን ይበልጥ የሚያበረታቱ የፖሊሲ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ ተባለ

ለሴት ሥራ ፈጣሪዎችን ይበልጥ የሚያበረታቱ የፖሊሲ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ ተባለ
• የብድር አቅርቦት ችግር ሊፈተሸ ይገባል
በይድነቃቸው ዓለማየሁ
ንግድ ምክር ቤቱ የዓለማቀፉን የሴቶች ቀን /ማርች 8/ ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የም/ ቤቱ ፕሬዝደንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ባስተላለፉት መልዕክት በአገራችን ታሪክ ሴቶች በኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እንዲሁም ተጠቃሚነት በጣም አናሳ ነው፡፡
ሴቶች በኢንቨስትመንት እና በሥራ ፈጠራ ላይ በስፋት እንዳይሳተፉ ማነቆ ከሆኑት ተግዳሮቶች መካከል የብድር አቅርቦት ችግር አንዱ ነው፡፡
በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተሰማሩ ሴቶች በብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ተኪ ምርቶችን ለሚያመርቱ እና የውጪ ምንዛሬ ለሚያስገኙ ማምረቻዎች ትኩረት መስጠቱ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ሴቶች በማንዩፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ያላቸውን አነስተኛ ተሳትፎ ለማሳደግ በሴቶች ላይ ያተኮሩ ፖሊሲዎችን በመፈተሽ ማበረታቻዎቸን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ፕሬዝደንቷ አሳስበዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ወ/ሮ ሃና አርአያሥላሴ በበኩላቸው መንግሥት በአገር በቀሉ የኢኮኖሚ ልማት ዕቅድ ውስጥ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን በማመን የግሉ ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡
በተለይም ሴቶች በአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መንግሥት የተለያዩ የሕግ እና የፖሊሲ እርምጃዎችን ወስዷል ብለዋል፡፡
ነገር ግን የሴቶች በኢንቨስትመንት በተለይም በማንዩፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ያላቸው ተሳትፎ በጣም አነስተኛ መሆኑን አሰታውሰው ይህንን እውነታ ለማሻሻል ኮሚሽን መ/ቤታቸው አዲስ ቻምበርን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
በሥነስርዓቱ ላይ ስኬታማ የሆኑ ሴት የቢዝነስ መሪዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች ወረቀት ያቀረቡ ሲሆን በተለይ ሴቶችን በሥራ ፈጠራ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዙሪያ ያሉ ዕድሎች እና ተግዳሮቶችን እንዲሆኑም ማነቆ የሆኑ ፖሊሰዎች እና አሰራሮች የጠቆሙ ሲሆን የመፍትሔ ሃሳቦችንም ሰንዝረዋል፡፡
ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች እና አሰተያየቶች የተሰጡ ሲሆን በአቅራቢዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
አዲስ ቻምበር የዘንድሮውን የዓለም ሴቶች ቀን ‘Women In Manufacturing’ በሚል መሪ ሃሳብ ማክበሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡