በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ተቋማት የቻይናን   “Big Market for All” እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀረበ።

የኢትዮ ቻይና የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡ በአዲስ ቻምበርና በቻይና ንግድ ሚኒስቴር ንግድ ልማት ቢሮ በተዘጋጀው የቢዝነስ ለቢዝነስ መድረክ ላይ በርካታ የኩባንያ መሪዎችና የቢዝነስ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

በቻይና የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ቀዳሚ ትኩረት ከሚሰጣቸው አገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን የቻይና ንግድ ሚኒስቴር የውጭ ንግድ ዲፓርትመንት ም/ዋና ዳይሬክተር ቻንግ ሁይ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ላኪዎች ጥራት ያላቸውን ምርቶች ማቅረብና የተወዳዳሪነት ደረጃቸውን ጠብቀው መቀጠል እንዳለባቸውና  የቻይና አስመጪዎች ጥራት ያላቸውን የኢትዮጵያ ምርቶችን በስፋት ለመግዛትና ዘላቂ የንግድ ድልድይ ለመገንባት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

((Big Market for All) በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የኢትዮ-ቻይና የቢዝነስ ለቢዝነስ (B2B) መድረክ ላይ የአዲስ ቻምበር ዋና ጸሐፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ መድረኩ ለንግድ ውይይት ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥ ላኪዎች ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያሻሽሉ፣ፈጠራን እንዲያሳድጉ እና ከቻይናውያን ሸሪኮቻቸው ጋር ልምድ እንዲለዋወጡ የሚረዳ ነው ብለዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ( ዶ/ር) በበኩላቸው በአገራቱ መካከል ያለውን የንግድ አለመመጣጠን ለማሻሻል የአገር ውስጥ ላኪዎች ምርቶቻቸውን በዓይነትና ጥራትን ከፍ አድርገው ማቅረብ  እንዳለባቸው ተናግረዋል። በቡና፣ በሶያ ቢን (አኩሪ አተር)፣ በቆዳና ሌጦ እንዲሁም በሰሊጥ ምርት ላይ የተሰማሩ ከ40 በላይ የአዲስ ቻምበር አባላትና የአገር ውስጥ ላኪዎች ከቻይና አቻዎቻቸው ጋር  የመግባቢያ ስምምነቶችን  ተፈራርመዋል፡፡  እነዚህ ስምምነቶች ከ340 ሚሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የንግድ ስምምነቶች እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አዲስ ቻምበር የግሉ ዘርፍ ድምጽ!