በ2015 ዓ፣ም የሚወጣው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ በአስጎብኚ ድርጅቶች ላይ የሚጥለው የተጨማሪ እሴት ታክስ በዜሮ ምጣኔ እንዲሰላ የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተርስ አሶሲየሽን ምክረ ሀሳብ አቀረበ፡፡

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ እድሎች እንዳሉት ሁሉ በርካታ ፈተናዎች አሉበት፡፡
የቱሪዝም ዘርፍ አንጻራዊ እድገት በማስመዝገብ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ካለው ሰፊ የቱሪዝምና የሰው ሀብት አንጻር ሲታይ ግን የሚፈለገው ውጤት እየተመዘገበ እንዳልሆነ በዚህ የስራ መስክ የተሰማሩ ዜጎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡
ዘርፉን ከሚገዳደሩ አበይት ተግዳሮች መካከል በዋናነት በአስጎብኚ ድርጅቶች የሚከፈል የተጨማሪ እሴት ታክስ አከፋፈል አንዱ ነው፡፡
የማስጎብኘት ስራ በዋናነት ከውጭ ሀገራት የሚመጡ ቱሪስቶችን በማስጎብኘት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ ከፍተኛ ሚና ቢኖረውም በ2015 አ.ም ይወጣል ተብሎ የሚታሰበው አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ግን የማስጎብኘት ስራ በዜሮ ታክስ ምጣኔ ከሚስተናገዱ ስራዎች ውስጥ እንዳልተካተተ የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተርስ ማህበር አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ከማስጎብኘት ስራ ውስብስብ ባህሪ አንጻር ሲታይም ለስራው በግብአትነት የሚያገልግሉ አብዛኛዎቹ ምርቶችና አገልግሎቶች በቱሪስት መዳረሻዎና የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ደረሰኝ ስለሌላቸው በታክስ አወሳሰንና አከፋፈል ላይ ከገቢ ሰብሳቢ አካላት ጋር አለመግባባቶች ለረጅም አመታት መቀጠላቸውን የገለጸው ማህበሩ ተወዳዳሪ የቱሪዝም ፖሊሲና ዘርፉ የሚመራበት የቱሪዝም ህግ ያለመኖር ዋና ምክንያት እንደሆነ ማህበሩ ስጋቱን ይገልጻል፡፡
በመሆኑም የማስጎብኘት ስራ በዋናነት የቱሪዝም አገልግሎትን በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ ጎብኚዎች በመሸጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ስራ በመሆኑ በ2015 አ.ም በሚወጣው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ እንደሌሎች በኤክስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ስራዎች የተጨማሪ እሴት ታክስ በዜሮ ምጣኔ እንዲሰላ ማህበሩ ምክረ ሀሳቡን አቅርቧል፡፡
ከዚህም ባለፈ ተወዳዳሪ የቱሪዝም ፖሊሲና ዘርፉ የሚመራበት ህግ እንዲኖር ፤ለማስጎብኘት ስራ በፖሊሲ ግብአትነት የሚያገለግል ሰነድ እንዲዘጋጅ በስራው ላይ ለተሰማሩ ህጋዊ የግል ተቋማት ሊያሰራ የሚችል መደላድል እንዲኖርና ህጋዊ አስጎብኚዎች እንዲበረታቱ ለአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ሀሳባቸውን አካፍለዋል፡፡
ከማስጎብኘት ስራ ባህሪ አንጻር አብዛኛዎቹ ግብአቶች ደረሰኝ የሌላቸው በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያግዝ የኦዲት ማኑዋል እንዲዘጋጅና አስጎብኚዎች የገቢ ግብር በማኑዋሉ መሰረት እንዲከፍሉ የሚመለከተው አካል ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው ማህበሩ ሀሳቡን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተርስ አሶሲየሽን 270 በማስጎብኘት ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን በአባልነት አካትቶ የያዘ ሲሆን ላለፉት 19 አመታት መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመተባበር የቱሪዝም ዘርፍ እድገት እንዲረጋገጥና ህዝቡ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ በማበርከት ላይ ይገኛል ፡፡
መንግስትም ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡