አዲስ ቻምበር ከቻይናው የሻንጋይ ንግድ ምክር ቤት ጋር በጋራ የሚሰራበትን የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ ።

በሻንጋይ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት የተመራ የንግድ ልኡካን ቡድን ከኢትዬጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ከአዲስ ቻምበር አመራሮችና አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል ።

የጋራ መግባቢያ ሰነዱን የአዲስ ቻምበር ፕረዚዳንት ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድ እና የሻንጋይ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ዋንግ ዢያኖሀን ተፈራርመዋል ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አምባሳደር ዝናቡ ይርጋ እና የአዲስ ቻምበር ተ/ዋና ፀሐፊ አቶ ዘካሪያስ አሠፋ ለልኡካን ቡድኑ የመክፈቻ እና የቁልፍ መልእክት ንግግር አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮምሽነር ዝናቡ ይርጋ በንግግራቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡ ፡

ምክትል ኮምሽነሩ ቻይናዊያን ባለሀብቶች በማኒፋክቸሪንግ፣በአግሮ ፕሮሰሲንግ ፣በፋርማሲቲካል፣ በጨርቃ ጨርቅ እና በአይሲቲ ዘርፎች ይበልጥ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት/ አዲስ ቻምበር/ ተ/ዋና ፀሀፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ መጠን ከ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ጠቅሰው ወደ ቻይና ያደላውን የንግድ ሚዛን ለማስተካከል ብዙ ስራ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል፡ ፡

ሁለቱ ንግድ ምክር ቤቶች በሁለቱ ከተሞች ያለውን ንግድና ኢንቨስትመንት ለማበረታታት ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ገልፀው ሁለቱ ንግድ ምክር ቤቶች በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል፡ ፡

የሻንጋይ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ም/ፕሬዚዳንት ሚስተር ዋንግ ዢያኖን በበኩላቸው የሻንጋይ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት እድል እንደሚጠቀሙና በቀጣይም በአዲስ ቻምበር በኩል የኢትዮጵያ ባለሀብቶች በሻንጋይ በመገኘት የንግድ ለንግድ ግንኙነት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ እንደሚመቻች ተናግረዋል፡ ፡

ሻንጋይ የቻይና ትልቋ የኢኮኖሚ፤የፋይናንስ እና የኢኖቬሽን ከተማ ስትሆን ጥቅል የከተማዋ የሀገር ውስጥ ምርት ከ 650 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡

#addischamber