በአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ የተመራ የቦርድና ማኔጅመንት አባላት አዲስ አበባ በሚገኘው የቻይና ኤምባሲ በመገኘት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ቺያን ሃይ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል ፡፡
ውይይታቸው በተለይም በአዲስ አበባና በተለያዩ የቻይና ከተሞች መካከል ያለውን የንግድ፣የገበያና የኢንቨስትመንት ትስስር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
የአዲስ ቻምበር አመራሮችን በኢትዮጵያ የህዝባዊት ሪፑብሊክ ቻይና አምባሳደር የሆኑት ሚስተር ቺያን ሃይ ተቀብለው በንግድና ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ዙሪያ አነጋግረዋል ።
አዲስ ቻምበርና አዲስ አበባ የሚገኘው የቻይና ኢምባሲ በቀጣይ የንግዱ ሕብረተሰብን እርስ በእርስ ለማገናኘት፣የንግድ እድሎችና መረጃዎች በመለዋወጥ፣ የንግድ ለንግድ ግንኙነት የሚፈጠርበት እንዲሁም የአዲስ ቻምበር የቦርድ አመራርና ሰራተኞችን በስልጠና አቅም ግንባታ በመስጠት የግሉን ዘርፍ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል ፡ ፡
የአዲስ ቻምበር አመራርና ሰራተኞች የረጅም ጊዜ የትምህርት ስኮላር ሺፕም እድልም ሆነ የአጭር ጊዜ ስልጠና በቻይና ሀገር የሚወስዱበትን ሁኔታ የሚመቻችላቸው መሆኑን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ቺያን ሀይ ለአዲስ ቻምበር የቦርድ አባላት ገልፀውላቸዋል፡ ፤
በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የተጠናከረ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን ለዚህም ማደግ የአዲስ ቻምበርና አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ ለረጅም አመታት ካላቸው አጋርነት አኳያ ለንግዱ ማደግ ሚናቸው ጉልህ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ፡፡
አዲስ ቻምበር ከዚህ በፊት በቻይና የተለያዩ ከተሞች ከሚገኙ ንግድ ምክር ቤቶች ጋር የተፈራረማቸው የመግባቢያ ሰነዶች እንዲሁም የነበረውን ግንኙነት በይበልጥ በማጠናከር ንግድና ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት ከኤምባሲው ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ተገልጿል ።
የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ መጠን እ.ኤ.አ በ2024 ከ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ ።
አዲስ ቻምበር ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመሆን በቅርቡ ከቻይና ሻንጋይ የሚመጡ ትልልቅ የንግድ ልኡካንን በመቀበል አዲስ አበባ ከሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ጋር ለማገናኘት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡ ፤