በአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ የተመራ የስራ አመራር አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ በመገኘት ከሚመለከታቸው ሀላፊዎች ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል ፡፡
ውይይታቸው በተለይም በአዲስ አበባና በተለያዩ የአሜሪካን ከተሞች መካከል ያለውን የንግድ፣የገበያና የኢንቨስትመንት ትስስር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
የአዲስ ቻምበር አመራሮችን በአሜሪካ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዬን መሪ ግዌንዶሊን ግሪን እና በኤምባሲው የንግድ ጉዳዮች ሀላፊ ሚስተር ሊዬን ስካርኒሺስኪ ከሌሎች የሚመለከታቸው ሀላፊዎች ጋር በመሆን ተቀብለው አነጋግረዋል ።
ሁለቱ ተቋማት (አዲስ ቻምበርና አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኢምባሲ) በቀጣይ የንግዱ ሕብረተሰብን እርስ በእርስ ለማገናኘት፣የንግድ እድሎችና መረጃዎች በመለዋወጥ፣ የንግድ ለንግድ ግንኙነት የሚፈጠርበት ሁኔታ በአጠቃለይ የግሉን ዘርፍ ለማሳደግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
በኢትዮጵያና በአሜሪካን መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እያደገ የመጣ ሲሆን በተለይም አዲስ ቻምበርና አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ ለረጅም አመታት ካላቸው አጋርነት አኳያ ለንግዱ ማደግ ሚናቸው ጉልህ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ፡፡
አዲስ ቻምበር ከዚህ በፊት በአሜሪካን የተለያዩ ከተሞች ከሚገኙ ንግድ ምክር ቤቶች ጋር የነበረውን ግንኙነት በይበልጥ በማጠናከር ንግድና ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት ከኤምባሲው ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ተገልጿል ።
የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ መጠን እ.ኤ.አ በ2024 ከ 1ቢሊየን ዶላር በላይ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ ።