ህዳር 24 2017 ዓ.ም
በአዲስ ቻምበር የዳሬክተሮች ቦርድ አባላት የተመራ የልኡካን ቡድን ተቀማጭነቱን በዱባይ ካደረገው አለም አቀፉ የቢዝነስ ተቋም ኢንቴግራ ሰቨን ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ዙሪያ በአጋርነት መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይቷል ፡፡
ልዑካን ቡድኑን በዱባይ ተቀብለው ያነጋገሩት የመንግስት እና የግል ዘርፉን በማማከርና በማገልገል የሚታወቀው የኢንቴግራ ሰባት ድርጅት መስራች እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናታሊያ ሲቼቫ ናቸው ፡፡
በአዲስ ቻምበር ፕሬዝዳንት መሰንበት ሸንቁጤ የተመራው ይሄው የልዑካን ቡድን በአባልነት ልማት ፣በአለም አቀፍ የንግድ ትስስርን ማጠናከር ፣አለም አቀፍ አጋርነትን ማጠናከር እና በዲጂታላይዜሽን ለውጥ ማምጣት በሚቻልበት ዙሪያ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል። በዚህም ‹‹አጋርነት ለጋራ ጥቅም ወሳኝ ነው›› ሲሉ ሁለቱም ወገኖች ተስማምተዋል።
ንግድ ምክር ቤቱ እያካሄደ ካለው የሪፎርም ሥራዎች አንዱ መሰል የሁለትዮሽ እና አለም አቀፋዊ አጋርነትን ማሳደግ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በዚህም በቢዝነስና ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ዙሪያ ከሚሰሩ የተለያዩ አለምአቀፍ መሰል ድርጅቶች ጋር ግንኙነትን ማጠናከር መጀመሩን እና እና ተሞክሮ መውሰድ መቻሉን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡ ፡
አዲስ ቻምበር እና የዱባይ ቻምበር ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር እ.ኤ .አ ህዳር 22 ቀን 2024 የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
ኢንቴግራ ሰቨን ኩባንያ የንግድ ድርጅቶችና መሪዎች ቀጣይነት ባለው ሽግግር ውሰጣዊ ለውጥን የሚቋቋሙ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚደግፍ አለም አቀፍ ድርጅት ነው ።
የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናታልያ እ.ኤ.አ. በ2019 በመካከለኛው ምስራቅ በሚታተመው የኢንተርፕረነር መፅሄት “ ለአደዲስ ቢዝነሶች አሰቻይ ስነ-ምህዳር ” በሚለው ምድብ የአመቱ ምርጥ የቢዝነስ ሴት የሚለውን ክብር አግኝተዋል ፡፡
በዱባይ ንግድ ምክር ቤት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን መስህብ እና የማስፋፊያ አጀንዳ በመቅረፅ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወቱ ይገኛል ፡፡