አዲስ ቻምበር ‘አዲሱ የውጪ ምንዛሬ ስርአት ለውጥ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ’ በሚል የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው፡፡

አዲስ ቻምበር ‘አዲሱ የውጪ ምንዛሬ ስርአት ለውጥ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ’ በሚል የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው፡፡
(ነሃሴ 10፤ 2016 ፤ አዲስ ቻምበር ) አዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ‘አዲሱ የውጪ ምንዛሬ ስርአት ለውጥ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ’ በሚል የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው፡፡
የፓናል ውይይቱን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቄጤ እንደተናገሩት ምክር ቤቱ በግሉ ዘርፍና በመንግሥት መካከል እንደ አገናኝ ድልድይ ሆኖ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል ለግሉ ዘርፍ አመቺ የሆኑ ህጎችና ፖሊሲዎች እንዲወጡለትና ተግባራዊ እንዲሆኑለት እንዲሁም አፈጻጻማቸው የተሳለጠ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ ምቹ የንግድ ከባቢ ሁኔታ ፤አመቺ አሰራሮችና ፖሊሲዎች እውን እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የግሉ ዘርፍ በግንባር ቀደምትነት ካስቀመጣቸው ለቢዝነስ ፈታኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካካል የብድርና የውጪ ምንዛሬ አቅራቦት ጉዳይ ከፍተኛውን ድርሻ መያዛቸውን በመድረኩ ላይ ጠቁመዋል::
በተለይ ምክር ቤታቸው ከኢትዮጵያ ቡና ማህበር ጋር በመተባበር ለውይይት ያቀረበው እና በቅርቡ በመንግስት እንዲተገበር ውሳኔ በተላለፈበት በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ሆኖ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን በጎም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖ የንግዱ ህብረተሰብ ግልጽ ግንዛቤ የሚያገኝበት መድረክ እንዲሆን በማሰብ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቷ አክለው እንደተናገሩት በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መዛባት ለማስተካከል ሚናው እስከምን ድረስ ነው፣ የገቢ እና የወጪ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ዋጋ ከገበያ እውነታዎች ጋር ለማጣጣም ምን ማድረግ ይገባል የሚሉት ጉዳዮች የውይይቱ አንኳር ነጥቦች ይሆናሉ ብለዋል።
የንግዱ ህብረተሰብ በዚህ ስርዓት ምን ይጠቀማል ምንስ ይጎዳል? የሸቀጥና የአገልግሎት ዋጋዎች በዚህ ስርዓት ምን ያጋጥማቸዋል? ይህ ትግበራ ብር፤ ዶላር፤ ዩሮ እና ፓውንድን ከመሳሰሉ ዋና ዋና የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለው የምንዛሬ ተመን እና ቁርኝት ወደፊትስ ምን ሊመስል ይችላል የሚሉት ጉዳዮች በተለያዩ ፓናሊስቶች የሚቀርቡ ይሆናል፡፡
በፓናል ውይይቱ የተለያዩ የመነሻ ጽሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን ከአቅራቢዎቹ መካከል ፕሮፌሰር አበበ ሽመልስ በገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ፤ አቶ አበባየሁ ዱፌራ በብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ሞኒተሪንግ እና ሪዘርቭ ማኔጅመንት ምክትል ዳይሬክተር ፤ አቶ እሸቱ ፋንታዬ የቢዝነስ ልማትና የፋይናንስ አማካሪ ፤ አቶ ጌታቸው ተክለማርያም በፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ኤንድ አካውንተቢሊቲ የፕሮግራም አስተባባሪ እና አቶ ይርጋ ተስፋዬ የኢኮኖሚ ተመራማሪ ይገኙበታል፡፡
አዲሱ የውጭ ምንዛሬ ማስተካከያን በተመለከተ የብሔራዊ ባንክ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መሀል; ቀደም ሲል በ38 የገቢ ንግድ ሸቀጦች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ መነሳቱ ፤ ወደ ውጭ የሚደረግ የካፒታል ሂሳብ ፍሰት እንደ በፊቱ የተገደበ ቢሆንም፤ የውጭ ምንዛሪ ገበያው ለገቢ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ነጻ የተደረገ ሲሆን ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች ካፈሩት የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለራሳቸው ያስቀሩት የነበረው 40 በመቶ ወደ 50 በመቶ ከፍ ማለት እና የመሳሰሉት ዋነኞቹ መሆናቸውን ከመድረጉ ለማወቅ ተችሏል ፡፡
የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ የመንግስትን ገቢ እና የውጭ ምንዛሪን በማሳደግ፣ የሀገሪቱን ጥቅል ምርት እንዲጨምር በማድረግ ረገድ አስተዋፅኦው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ተጠቁሟል፡፡
ይሁን እንጂ እየተስተዋለ ያለው የዕዳ ጫና፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፤ገና ብዙ ሥራ የሚፈልገው የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት፣ አዝጋሚ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ፣ ዝቅተኛ የዘርፎች ምርታማነት፣ ዝቅተኛ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸምና የሀብት ብክነት፤ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች መሆናቸው ተገልጿል ።
በመድረኩ ላይ አስመጪና ላኪዎችን ጨምሮ ከ 100 በላይ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ፡፡