በንግድ ትርኢቱ በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ የሃገር ውስጥ እና የውጭ ነጋዴዎች ተሳታፊ ሆነዋል::
ንግድ ትርኢቱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ተወካይ አቶ መከታ አዳፍሬ፡የኢትዮጵያ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው እንዲሁም የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ በጋራ በመሆን አስጀምረውታል፡፡
ንግድ እና ኢንዱስትሪ በመንግስት ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ መሆኑን በንግግራቸው ያነሱት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ተወካይ ዘርፉ በበርካታ ችግሮች የተከበበ ቢሆንም መንግስት በመሰረተ ልማት፡ በሎጀስቲክስ፡በቴክኖሎጂ እና በሌሎችም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአዳዲስ የቴክኖሎጂ መሰረተልማት ስራዎች ላይ በመንግስት የተሰጠው ትኩረት ንግድን ለመከወን አወንታዊ ድርሻው ሰፊ መሆኑን በንግግራቸው ያነሱት የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም የግሉ ዘርፍ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ አሁንም እገዛ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል::
አክለውም ለቴክኖሎጂ እና አዳዲስ ፈጠራዎች መስፋፋት ለሚገጥሙ እንቅፋቶች የፖሊሲ ማሻሻያዎች ፡የባለድርሻዎች ተቀናጅቶ መስራት ችግሮቹን ለመቅረፍ እና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚያግዙ ያነሱ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ንግድ ምክር ቤቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች እና የሚያዘጋጃቸው ንግድ ትርኢቶች እገዛ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡
ለአምስት ቀን በሚቆየው ንግድ ትርኢትም ተሳታፊዎች ራሳቸውን ለማስተዋወቅም ሆነ አዳዲስ አሰራሮችን እንዲቀስሙ እንዲሁም የገበያ እድሎችን ለማግኘት እድል ዕንደሚፈጥርላቸው ይጠበቃል፡፡