ሀገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት አመቻችነት ከንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር መክሯል ። ኮሚሽኑ ሁሉን አቀፍ የምክክር መድረክ ለማድረግ ዝግጅት ላይ ሲሆን የንግዱ ማህበረሰብንም ያካትታል ተብሏል ። በቅርቡ በሀገሪቱ ሰላምና እርቅን ለማስፈን ይደረጋል በተባለው የምክክር መድረክ ላይ ከንግዱ ማህበረሰብ መሪ ሀሳቦችን ማቅረብ እና ንቁ ተሳትፎ ይጠበቃል ተብሏል። የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሠንበት ሸንቁጤ ንግድን ለማሳለጥ ሰላም ወሳኝነት አለው ያሉ ሲሆን ም/ቤቱ በምክክር ሒደቱ ውስጥ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል ።
በውይይቱ ላይ የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሀመድ ድሪር ፤ ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ፤ የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሠንበት ሸንቁጤ እና ዋና ጸሀፊው አቶ ሺበሺ ቤተማርያም እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል ። የም/ቤቱ ዋና ጸሀፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በበኩላቸው የኮሚሽኑን አላማ የሚደግፍ ” ሰላም ለቢዝነስ ቢዝነስ ለሰላም ” በሚል ርእስ በቅርቡ የውይይት መድረክ የማድረግ እቅድ እንዳለው ጠቁመዋል ።