የዲጂታል ግብይትን ለማሳደግ የህግና የቁጥጥር ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ባዘጋጀው የመንግስት እና የግሉ ዘርፍን ባገናኘው የውይይት መድረክ ላይ በ I T ዘርፍ የተሰማሩ የሃገር ውስጥ ድርጅቶች ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡
የዲጂታል ኢኮኖሚው ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ባህሪውን ያገናዘበ ቁጥጥር እና አሰራር እንደሚያስፈልገው በተነሳበት ውይይት ላይ የመንግስት ባለሞያዎች ፣በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ሃገራዊ የገበያ ትስስር መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተከትሎ የዲጂታል ግብይቱ በሃገር ውስጥ የንግድ ዘርፍ ላይ ከሚያሳድረው ጫና ለማምለጥ ዝግጁነት ወሳኝ መሆኑ ተነስቷል፡፡
በውይይቱ የአፍሪኮም ቴክኖሎጂ ስራ አስኪያጅ ባህሩ ዘይኑ ፣ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዶ/ር አብዮት ባዩ እንዲሁም ከንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ወ/ት ሳራ ሰይፉ በICT ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከአፍሪካ ነጻንግድ ቀጠና ተጠቃሚ ለመሆን መዘጋጀት ስላለባቸው ሁኔታ ፣የዲጂታል ግብይት የቁጥጥር አሰራሮች እና የሃገራችን ዝግጁነት ላይ ያተኮሩ ለውይይት መነሻ የሆኑ ጽሁፎችን አቅርበዋል፡፡
ከዲጂታል ግብይት ጋር በተያያዘ መሰረተ ልማት አለመሟላት ፣ከሃገር ተሻጋሪ የሆኑ የኢኮሜርስ የክፍያ አሰራሮች አለመኖር፣ የICT ህጎቻችን ከሌሎች ሃገሮች አንጻር መፈተሸ መፈለጋቸው እንዲሁም ከመረጃ ጥበቃ ጋር የተያያዙ ክፍተቶች በቀጠናዊ ግብይቱ ተጠቃሚ ለመሆን እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ መሆናቸው የተነሳ ሲሆን ፡ለዚህም ጠንካራ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ቅንጅት፡ቀጣይነት ያለው ቀጠናዊ ትስስሩን ማእከል ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንዲሁም ንግድን ለመከወን የሚወጣው ወጭ ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ መሻሻሎች እንዲኖሩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል::
የዲጂታል ግብይት ስርአት ከግዜ ወደግዜ ማደጉን ተከትሎ ካስከተላቸው እና ትኩረት ብሎም ቁጥጥር ስራ ካስፈለጋቸው መካከል የመረጃ እና የደህንነት ስጋት፣የአይምሮአዊ ንብረት እና የደንበኞች ጥበቃ እንዲሁም ያልተገቡ ውድድሮች እንዲፈጠሩ ማድረጉ ከተጠቀሱት መካከል ጥቂቶቹ ሲሆኑ እነዚህን እና የዲጂታል ግብይት ባህሪን ተከትለው ለሚመጡ ስጋቶች የቁጥጥር አሰራሩ መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
የዲጂታል ኢኮኖሚው ድንበር የለሽ እየሆነ መምጣቱን እና በፍጥነት መቀያየሩን ተከትሎ እንዲሁም አዳዲስ የንግድ ሞዴሎች ቶሎቶሎ መምጣታቸው ህጎቹን ለመፈፀም እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ተነስቷል፡፡
ለዚህም የዲጂታል ግብይትን አስመልክቶ እንደባህሪው የቁጥጥር እና የህግ ማእቀፎች ቶሎ ቶሎ መቀየር እንደሚኖርባችው ተጠቅሷል፡፡
የዲጂታል ግብይትን ለማሳደግ እና በዘርፉ የተሰማሩት በሃገር ውስጥም ሆነ በአሃጉራዊ ንግድ ቀጠናው ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ የተቋማት መቀናጀት እና ተናቦ መስራት ወሳኝ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡