Addis chamber: November 29,2024
በውይይቱ ከብሄራዊ ባንክ የውጭ ኢኮኖሚ ትንተና እና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ወርቅነህ የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያው ካስገኛቸው ጥቅሞች ውስጥ በህጋዊ እና በህገውጥ የውጭ ምንዛሬ ተመን መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ መምጣት፣በህጋዊ መንገድ የሚላክ የሃዋላ ፍሰት መጨመር እና ለአምራች ድርጅቶች የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት መሻሻል እንዲሁም የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ክምችት መጎልበትን የጠቀሱ ሲሆን በማሻሻያው ተገኘ ያሏቸው አበረታች ውጤቶች ዘላቂ እንዲሆኑ እና ወደፊት የሚገጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በውይይቱ ማሻሻያው በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያለውን ዕድሎች እና ተግዳሮቶች ላይ በማተኮር የውይይት መነሻ ያቀረቡት የአዋሽ ባንክ የትራንስፎርሜሽን ዳይሬክተር አቶ ቴድሮስ ሃይሉ ሲሆኑ ማሻሻያው ካስከተላቸው ስጋቶች ውስጥ በባንኮች መካከል ያለን እንዲሁም ከውጭ ከሚገቡት ጋር የመወዳደር አቅም መቀነስ፡አዳዲስ ክህሎቶችን መፈለግ ለምሳሌ የውጭ ምንዛሬ ተመን መወሰን እና መደራደር እንዲሁም አስተዳደር እና ትንበያ፡ ከአሰራር ጋር በተያያዘም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመግዛት ወጭን መጨመር እና ሌሎችንም ያነሱ ሲሆን፡ መልካም አድሎች ከሏቸው ደግሞ ለግሉ ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እና የባንኮችን የውጭ ምንዛሬ ሃብት መጨመር፣ከደንበኞች የሚመጡ አላስፈላጊ ጫናዎችን መቀነስ እንዲሁም የአለም አቀፍ የንግድ ክህሎቶችን ለመማር ለባንኮች እድል መፍጠሩን እና ሌሎችንም አንስተዋል፡፡
ለብሄራዊ ባንክ ካቀረቡት ምክረ ሃሳብ መካከልም አዳዲስ የግብይት መሳርያዎችን መፍቀድ እንዲሁም የባንኮችን ተወዳዳሪነት ለመጨመር ካፒታላቸው እንዲጨምር ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በቀረበው የውይይት መነሻ ጽሁፍ ላይ በማተኮር ከተሳታፊዎች አስተያየት እና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ከጽሁፍ አቅራቢዎቹም ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡