የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት የአለም አቀፉን የንግድ ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ በቢሯቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡ ፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት / አዲስ ቻምበር/ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድና ሌሎች የቦርድ አባላት ለረዥም አመታት ምክር ቤቱ አባል ከሆነበት ከአለም አቀፉ የንግድ ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ ሚስተር ጆን ዴንቶን ጋር በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡ ፡

ውይይታቸው በሁለቱ ንግድ ምክር ቤቶች መካከል ያሉትን እድሎችን በመጠቀም ተቀራርበው ለመስራት ያለመ ነው፡፡

የአለም አቀፉ ንግድ ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ በውይይታቸው እንደተናገሩት አዲስ ቻምበርና መቀመጫውን ፓሪስ ያደረገው የአለምአቀፉ ንግድ ምክር ቤት ጋር ያለው ግንኙነት ረዥም አመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው ሁለቱ ምክር ቤቶች በሀገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ሁኔታ ንግድና ኢንቨስትመነትን ለማስፋፋት የአቅም ግንባታ ስራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡ ፡

ኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መቀመጫ እንደመሆኗ እና በጥቅል ሀገራዊ ምርቷ/ ኢኮኖሚዋ/ ተጠቃሽ እየሆነች መምጣቷ የአለም አቀፉን ንግድ ምክር ቤት ቀልብ እየሳበው መጥቷል ብለዋል፡ ፡

በሀገሪቱ በተለይም በከተማዋ ያለውን የንግድ ማህበረሰብ ከአለም አቀፉ ንግድ ጋር ለማስተሳሰር የአለም አቀፉ ንግድ ምክር ቤት ከአዲስ አበባው ንግድ ምክር ቤት ጋር በጋራ ይሰራል ብለዋል፡ ፡
የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ በበኩላቸው ንግድ ምክር ቤታቸው ለረጅም አመታት የነበረውን ግንኙነት በመጠቀም ተጨባጭ ወደ ሆኑ የንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች ለመለወጥ እና ከአለም አቀፉ ንግድ ምክር ቤት ጋር በጋራ እንደሚሰሩና ቁርጠኛ መሆናቸውን ለዋና ፀሃፊ ሚስተር ዴንቶን ገልፀውላቸዋል፡ ፡

የአዲስ ቻምበር ተ/ዋና ፀሃፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ ለአለም አቀፉ ንግድ ምክር ቤት ዋና ፀሃፊና ልኡካኖቻቸው ስለ ንግድ ምክር ቤቱ እንቅስቃሴና ስለ ንግድ ከባቢ ሁኔታው ገለፃ አድርገዋል፡ ፡

የአለም አቀፉ ንግድ ምክር ቤት በስሩ ወደ 170 ሀገራት ያሉ የተለያዩ ንግድ ምክር ቤቶችን ያቀፈና ከ 45 ሚሊዮን ኩባንያዎችን በላይ በአባልነት የያዘ የ 106 አመት እድሜ ያለው ንግድ ምክር ቤት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡ ፡