የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ በከተማዋ ከሚገኙ የተለያዩ የንግድ ማህበራት መሪዎች ጋር ምክክር አካሄዱ፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት/ አዲስ ቻምበር/ በርካታ የሪፎርም ስራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን ከነዚህ ስራዎች መካከል የምክር ቤቱን አደረጃጀትና አገልግሎት በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ ተደራሽ በማድረግ አቃፊ የሆነ የንግድ ድጋፍ አገልግሎትን ለመስጠት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

ይህንን ሰፊ የሪፎርም ስራ ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳው ዘንድ ምክር ቤቱ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ሲሆን ከነዚህም መካከል የ5 አመት የስትራቴጂክ እቅድን በመንደፍ የንግዱ ማህበረሰብ አቅም የሚገነባበትን፤ጥቅሙና ፍላጎቱ የሚከበርበትን አሰራር መዘርጋት ዋናው ጉዳይ ሆኗል።

በዚህም የምክር ቤቱን አደረጃጀትና አገልግሎት አመቺና ውጤታማ በሆነ መልኩ በመዘርጋት፤ ከአለምአቀፍና ከአገር ውስጥ አጋር አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከርና በጋራ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙርያ አብሮ መስራት እንዲሁም የተበታተኑ አሰራሮችን ወደ አንድ በማምጣት በጋራ ውጤትን ማስመዝገብ የሚሉት ጉዳዬች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ።

በተለይም ምክር ቤቱ በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የንግድ ማህበራትን በአንድ ጥላ ስር በማሰባሰብ ሀብትና ጉልበትን በአንድ ላይ በማጣመር ስልታዊ በሆነ መልኩ የጋራ ግብን ማሳካት እንደ አንድ ስትራቴጂክ አቅጣጫ በመውሰድ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ እሮብ ሰኔ 11 2017 አ.ም ከተለያዩ የንግድ ማህበራት መሪዎች ጋር ሰፋ ያለ ውይይትን አድርገዋል፡፡

በዚህ የውይይት መርሀ ግብር ላይ የአትክልት ነጋዴዎች ማህበር ፣ የልኳንዳ ነጋዴዎች ማህበር፣ የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማህበር፣ የዳቦ አምራች ማህበር፣ የእህልና ወፍጮ ነጋዴዎች ማህበር እና የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ማህበር አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

በውይይታቸውም አዲስ ቻምበር ትክክለኛ የነጋዴ ድምጽ መሆን የሚችለው ከመሰል ማህበራት ጋር በጋራ በመሆን እና በአንድ ጥላ ስር መሰባሰብ ሲቻል ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የነበሩ የተለያዩ ማህበራት የንግዱን ማህበረሰብ መብትና ጥቅም ለማስከበር ያደረጉትን ጥረት ያደነቁት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ አሁን ላይ ደግሞ የተጀመሩ ጥረቶችን በትብብር፤ በአንድ ጥላ ስር በመሰባሰብ እንዲሁም ስልታዊ በሆነ መልኩ ውጤታማ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ምክረ ሀሳባቸውን ለግሰዋል፡፡

በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ስለ ምክር ቤቱ አሰራርና አገልግሎት በምክር ቤቱ ተ/ ዋና ጸሀፊ በአቶ ዘካርያስ አሰፋ የቀረበ ሲሆን በተለይም ከተለያዩ የነጋዴዎች ማህበራት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን በውይይት መድረኩ ላይ ገልፀዋል ፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ምክር ቤቱ ያለውን ልምድ፤ እምቅ እውቀትና አደረጃጀት ተጠቅሞ ከዚህ ቀደም በተናጠልና በተበታተነ አካሄድ ሲሰሩ የነበሩ የንግድ ድጋፍ አገልግሎቶችን አሁን ላይ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመስራት እድልን እንደሚፈጥር በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የማኔጅመንት አመራሮች ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በነበረው የውይይት ሂደት ላይ ተሳታፊ የነበሩ የንግድ ማህበራት መሪዎች ከዚህ ቀደም የነበሩ የተናጠል አካሄዶችና ጥረቶች ለንግዱ ማህበረሰብ የተፈለገውን ውጤት እንዳላመጡ ነገር ግን በአዲስ ቻምበር ጥላ ስር መሰባሰብና በቅንጅት መስራት ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡