የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ከ75ኛው ክብረ በዓል ንግግር የተወሰደ

” የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከተመሰረተበት 1939 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ዘመናት በርካታ ተግዳሮቶችን አልፎ ተቋማዊ ህልውናውን አስጠብቆ ላለፉት 75 ዓመታት የተጓዘ ሀገራዊ ተቋም ነው፡፡
ምክር ቤታችን 75ኛ የምስረታ በዓሉን ሲያከብር ለበርካቶች የሚያካፍለው ልምድ ሰንቆ የራሱንም አቅም በጠንካራ መሰረት ላይ እየገነባ ነው ፡፡
በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የንግድ ምክር ቤቶች ታሪክ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፍው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፋና ወጊ ብቻ ሳይሆን በስራዎቹም አርአያ ለሌሎችም ምክር ቤቶች መቋቋም መሰረት ነው ማለት እንችላለን፡፡ ”
የአዲስ ቻምበር ዋና ፀሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም ከ75ኛው ክብረ በዓል ንግግር የተወሰደ
” አዲስ ቻምበር እድሜ ጠገብ ተሞክሮዎቹን ነቅሶ እና ፈትሾ ፣አገልግሎቶቹን አዘምኖና ለአባላቱ ተደራሽና እውነተኛ ድምፅ በመሆን በመረጃ የተደገፉ አማራጭ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክረ ሀሳቦችን በመስጠት በሁሉም መንገድ የመፍትሄ አካል በመሆን የመስራች አባቶቻችንንና እናቶቻችንን አደራ የማስቀጠል ግዴታ አለብን፡፡
75ኛ አመት በዓል ስንዘክር ንግድ ምክር ቤታችን የንግዱን ማህበረሰብ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ የሄደበትን ርቀት እና ትጋት ለአሁኑ ትውልድ እንዲያመላክት ለማድረግ ጭምር ነው፡፡ ”
የኢፌዲሪ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሀሰን መሃመድ ከ75ኛው ክብረ በዓል ንግግር የተወሰደ
” አዲስ ቻምበር ለሚያከናውናቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ተግባራት ውጤታማነት የሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ከጎናችሁ እንደሆነ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ በተለይም በአፍሪካ ቀጠናዊ ነፃ ገበያ በተፈጠሩና ሊፈጠሩ በሚችሉ አመቺ መልካም አጋጣሚዎች እና እድሎች ዙርያ የግሉን ዘርፍ ሚናና አስተዋፅኦ ለማጎልበት አብረን የምንሰራ መሆኑን እገልጻለሁ ”