አዲስ ቻምበርና የአለም አቀፉ የግሉ ዘርፍ ኢንተርፕራይዝ ማእከል በግሉ ዘርፍ ልማት ዙርያ አብረው ለመስራት የሚያስችላቸውን ውይይት አካሄዱ

የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ የአለም አቀፉን የግል ኢንተርፕራይዝ ማእከል/ CIPE/ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተርና አመራሮችን በቢሯቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡ ፡

ሁለቱ ተቋማት በመሪዎቻቸው አማካኝነት በኢትዮጵያ ምቹ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ምህዳር እንዲፈጠር የሚያስችሉ የጋራ መድረኮችን በማዘጋጀት ለግሉ ዘርፍ ምቹ የሆኑ ፖሊሲዎችና ህጎች እንዲተገበሩ የጋራ ስራዎችን ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በውይይታቸው የምክር ቤቱ ፕረዚደንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ ፤ የምክር ቤቱ ዋና ጸሀፊ መሰረት ሞላ (ዶ/ር) እንዲሁም የሳይፕ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር አቶ ኀይለመለኮት አስፋው እና የሳይፕ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ለንግዱ ህብረተሰብ ማደግ የንግድ ምክር ቤቶች ሚና ወደር የለውም ያሉት የሳይፕ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር አቶ ኀይለመለኮት አስፋው የንግድ ምክር ቤቶችን በፋይናንስና በቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ የሚያደርጉትን እገዛ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

ላለፉት ረጅም አመታት ሳይፕ እንደ አዲስ ቻምበር የመሳሰሉ ተቋማትን በመደገፍ በግሉ ዘርፍና በመንግስት መካከል የጋራ የምክክር መድረክ እንዲፈጠር፤ ንግድና ኢንቨስትመንት ፖሊሲዎች እንዲዳሰሱና እንዲስተካከሉ ጥረት መደረጉን አቶ ኀይለመለኮት ተናግረዋል፡ ፡

በቀጣይም በተመረጡ ንግድ ነክ አጀንዳዎች ላይ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የፖሊሲ አድቮኬሲ የውይይት መድረኮች እንደሚዘጋጁ አክለው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሀመድ በበኩላቸው አለም አቀፉ ግል ኢንተርፕራይዝ ማእከል እስከ ዛሬ ድረስ ምክር ቤቱን ለማገዝ ያደረገውን ጥረት ያደነቁ ሲሆን አመቺ ፖሊሲዎችና አሰራሮች እውን እንዲሆኑ አሁንም ቢሆን ተቋሙ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተለይም የንግድና ኢንቨስትመንትን ተግዳሮቶችን ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ምክር ቤቱ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

አዲስ ቻምበር የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት ከአነስተኛ ቢዝነሶች እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ የንግድ ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ስራ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤቱ ዋና ጸሀፊ መሰረት ሞላ (ዶ/ር) ማእከሉ የንግዱን ማህበረሰብ እና ምክር ቤቱን ለማገዝ የሚያደርገውን ጥረት ያደነቁ ሲሆን አዲስ ቻምበር አጋርነትን እንደ አንድ የትኩረት አቅጣጫ በመያዝ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን በመፍጠር ምክር ቤቱ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲስ ቻምበር በቅርቡ ከማእከሉ ጋር በመተባበር በታክስና በጉምሩክ ሪፎርም ዙሪያ ትልቅ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ማካሄዱ ይታወሳል፡ ፡