ንግድ ም/ቤቱ የኤክስፖርት ማቀላጠፊያ ፖርታል አስጀመረ • ፖርታሉ አባል የላኪዎችን መረጃዎችን ይዟል፤

ንግድ ም/ቤቱ የኤክስፖርት ማቀላጠፊያ ፖርታል አስጀመረ
• ፖርታሉ አባል የላኪዎችን መረጃዎችን ይዟል፤
በይድነቃቸው ዓለማየሁ
አዲሱ አገልግሎት የም/ቤቱ አባላት በተለይም ላኪዎች ወጪ ንግዳቸውን ለማሳለጥ የሚያስፈጉ የገበያ መረጃዎችን፤ሠነዶችን ፤መመሪያዎች ፤ ዓለማቀፍ የጥራትና የደረጃ መስፈርቶችን በፖርታሉ ላይ ከአንድ ቦታ ተሰድረው ማግኘት እንዲችሉ ይረዳል ተብሏል፡፡
በሥነሥርዓቱ ላይ የንግድ ም/ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም የዚሁ ፖርታል ዝግጅት ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ በዓለማቀፍ ንግድ ላይ የተሰማሩ አባላቱን ድጋፍ ለማድረግ ተስቦ ነው ፡፡
በአገልግሎቱ በተለይም ላኪዎች የገበያ መረጃዎች የሚለዋወጡበት፤የቢዝነስ ሃሳቦችን የሚጋሩበት፤ ካሉበት ቦታ ሆነው የንግድ ሸሪኮችን በቀላሉ ማፍራት እንዲችሉ ያግዛል ብለዋል፡፡
ለፖርታል አገለግሎት እንዲጀመር ድጋፍ ያደረገው (ጂ አይ ዜድ) የተሰኘው የጀርመን መንግሥታዊ ተራድኦ ድርጅት ተወካይ ወ/ሮ አረጋሽ አስፋው በበኩላቸው ድርጅቱ የግሉን ዘርፍ አቅም በመገንባት በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን አበርክቶ ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ነው፡፡
ይህ አዲስ ዲጂታል አገልግሎት እንዲጀመር የተደረገው ድጋፍ የዚሁ አካል ነው ብለዋል፡፡
ስለ ፖርታሉ አጠቃቀም በባለሙያዎች ገለጻ የተደረገ ሲሆን በዚህ መሠረት ፖርታሉ የላኪ ድርጅቶችን መረጃ፤ የሚልኩትን ምርት እና አገልግሎት ፤ በዘርፍ በዘርፍ ለይቶ መረጃ የሚሰጥ ሲሆን በውጪ ለሚገኙ ተቀባዮች በቀላሉ የቢዝነስ ግንኙነት አንዲጀምሩ ይጋብዛል፡፡
ይኸው ፖርታል በንግድ ም/ቤቱ ድረ-ገጽ(www.addischamber.com) ላይ ከፍትለፊት የሚገኝ ሲሆን ለአባላቱም ሆነ ማንኛው ነጋዴ አገልግሎት አንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡