ንግድ ምክር ቤቱ የፋይናንስ ዘርፉን መረጃ ብቻ የያዘ አልማናክ እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ::

የፋይናንስ ዘርፉ ለኢኮኖሚው መሻሻል እንዲሁም ለንግድ እና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ሚናው ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ንግድ ምክር ቤቱ በተለያዩ አገልግሎቶች ዘርፉን ሲደግፍ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
በሃገራችን ውስጥ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት የተደራጀ መረጃዎችን እንዲሁም ወቅታዊ የሆኑ ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን እንዲይዝ ተደርጎ በምክር ቤቱ የሚዘጋጀው አልማናክ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ባለሃብቶች የሃገር ውስጥ የፋይናንስ እድገትን የሚያመላክቱ መረጃዎችን የሚያገኙበት፣የቴክኖሎጂ መሻሻሎችን፣አዳዲስ አሰራሮችን እንዲሁም ከዘርፉጋር የተገናኙ የጥናት ውጤቶችን የሚያገኙበት ተደርጎ የሚዘጋጅ ነው ተብሏል፡፡
የሚዘጋጀው አልማናክ የሞባይል መተግበርያ ያለው በመሆኑ፡ተደራሽነቱን ለመጨመር እንደሚረዳው ተጠቁሟል፡፡
ባንኮች ኢንሹራንሶች ፣አነስተኛ የብድር ተቋማት፣የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎች እና በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ያሉትን ያካትታል፡፡
ምክር ቤቱ በሚያዘጋጀው አልማናክ ላይ የሚሳተፉ የፋይናንስ ተቋማት አዳዲስ አገልግሎቶቻቸውን የምክር ቤቱ ተደራሽነት ባለበት ሁሉ ለማስተዋወቅ የሚያግዛቸው ሲሆን ከሃገር ውስጥ አልፎ በሌሎች ሃገሮችም ደንበኞችን ለማፍራት አይነተኛ መንገድ እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡
አልማናኩ በኢሊሊ ሆቴል በተዋወቀበት ወቅት የተጋበዙት የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች ይህ የቢዝነስ ማስታወቅያ አልማናክ አገልግሎታቸውን ለሚመለከታቸው አካላት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳቸው እና በእትሙም እንደሚሳተፉ ገልፀዋል፡፡