ንግድ ምክር ቤቱ አባላቶቹን እና አጋሮቹን አመሰገነ

ከተመሰረተ 78 አመት ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላቱን አና በተለያየ ወቅት ምክር ቤቱን ያገለገሉትን እንዲሁም አጋሮቹን አመስግኗል፡፡

ምክር ቤቱ እዚህ ለመድረሱ አባላቱ ትልቅ ድርሻ አላቸውም ተብሏል፡፡ በዝግጅቱ ላይ የምክር ቤቱ የቦርድ አባላት በተለያየ ደረጀ ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር በአጋርነት ሲሰሩ የቆዩ የሃገር ውስጥም ሆነ የውጭ ደርጅቶች እንዲሁም አባላቶቹ እና ጥሪ የተደረገላቸወ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ የምስጋና ስነ ስርዐቱን በማስመልከትም በሃገራችን የተወሰደው የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ እና ቁልፍ ውጤቶች እንዲሁም በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያለው እንድምታን አስመልክቶ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ከብሄራዊ ባንክ የውጭ ኢኮኖሚ ትንተና እና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ወርቅነህ የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያው ካስገኛቸው ጥቅሞች ውስጥ በህጋዊ እና በህገውጥ የውጭ ምንዛሬ ተመን መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ መምጣት፣በህጋዊ መንገድ የሚላክ የሃዋላ ፍሰት መጨመር እና ለአምራች ድርጅቶች የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት መሻሻል እንዲሁም የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ክምችት መጎልበትን የጠቀሱ ሲሆን በማሻሻያው ተገኘ ያሏቸው አበረታች ውጤቶች ዘላቂ እንዲሆኑ እና ወደፊት የሚገጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በውይይቱ ማሻሻያው በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያለውን ዕድሎች እና ተግዳሮቶች ላይ በማተኮር የውይይት መነሻ ያቀረቡት የአዋሽ ባንክ የትራንስፎርሜሽን ዳይሬክተር አቶ ቴድሮስ ሃይሉ ሲሆኑ ማሻሻያው ካስከተላቸው ስጋቶች ውስጥ በባንኮች መካከል ያለን እንዲሁም ከውጭ ከሚገቡት ጋር የመወዳደር አቅም መቀነስ፡አዳዲስ ክህሎቶችን መፈለግ ለምሳሌ የውጭ ምንዛሬ ተመን መወሰን እና መደራደር እንዲሁም አስተዳደር እና ትንበያ፡ ከአሰራር ጋር በተያያዘም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመግዛት ወጭን መጨመር እና ሌሎችንም ያነሱ ሲሆን፡ መልካም አድሎች ከሏቸው ደግሞ ለግሉ ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እና የባንኮችን የውጭ ምንዛሬ ሃብት መጨመር፣ከደንበኞች የሚመጡ አላስፈላጊ ጫናዎችን መቀነስ እንዲሁም የአለም አቀፍ የንግድ ክህሎቶችን ለመማር ለባንኮች እድል መፍጠሩን እና ሌሎችንም አንስተዋል፡፡ለብሄራዊ ባንክ ካቀረቡት ምክረ ሃሳብ መካከልም አዳዲስ የግብይት መሳርያዎችን መፍቀድ እንዲሁም የባንኮችን ተወዳዳሪነት ለመጨመር ካፒታላቸው እንዲጨምር ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በቀረበው የውይይት መነሻ ጽሁፍ ላይ በማተኮር ከተሳታፊዎች አስተያየት እና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ከጽሁፍ አቅራቢዎቹም ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ባዘጋጀው የምስጋና ቀን ላይ በአባልነት ረዥም ግዜ ያስቆጠሩ ነጋዴዎች እንዲሁም በአጋርነት የሰሩ ድርጅቶች ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር የነበራቸውን የስራ ግንኙነት የተመለከተ ምስክርነታቸውን የሰጡ ሲሆን፡በአባላት ልማት እና በዲጂታላይዜሽን፣ለግሉ ዘርፍ በፋይናስ ተደራሽነት እንዲሁም በስልጠና እና ንግድ ልማት አገልግሎት ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የስምምነት ሰነድም በምክር ቤቱ እና በአዋሽ ባንክ መካከል ተፈርሟል፡፡ የምክር ቤቱ ፕረዚደንት በመዝጊያ ንግግራቸው እንደገለጹት ምክር ቤቱ በለውጥ ሂደት ላይ መሆኑን እና በቀጣይ ጊዜያት አሁን ካለበት በላይ መሆን እንዲችል ይበልጥ ተወዳዳሪ እንዲሆን የንግዱ ማህበረሰብ ከጎኑ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡