በሀገራዊ የንግድ ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ዙርያ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የውይይት መድረክ ተካሄደ።

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ላይ የንግዱ ዘርፍ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም የንግድ ዘርፉ የሚመራበት ራሱን የቻለ ፖሊሲ አለመኖር የገቢ ንግዱ ወጥ በሆነ እሳቤ እና አደረጃጀት የሚመራ አለመሆኑ እንዲሁም የወጪ ንግዱም ቢሆን በበርካታ ተቋማት የሚመራና ቅንጅትና መናበብ የሚጎድለው ሆኖ መቆየቱ በውይይት መድረኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህም ባለፈ የንግድ ስርአቱ ፍትኀዊ ውድድር የሚጎድለዉና በይበልጥ በአለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ያላረጋገጠ ዘርፍ ሆኖ ቆይቷል ፡፡

እነዚህን ክፍተቶች በመገንዘብ ባለፉት አመታት ዘርፉን ለማዘመንና ተወዳዳሪ ለማድረግ ሲከናወኑ ከቆዩት የንግድ ሪፎርም አጀንዳዎች መካከል በዘርፉ የሚታዩ መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታትና አለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ብሄራዊ ፖሊሲ እንዲኖረው ማስቻል ትኩረት ተሰጥቶት ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ከሳሁን ጎፌ( ዶ/ር) የውይይት መድረኩን በይፋ በከፈቱበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

የንግድ ፖሊሲው መንግስት በሀገር ውስጥና በውጭ ንግድ መስኮች ላይ ለሚተገብራቸው አጀንዳዎች እና ለሚወስዳቸው እርምጃዎች ግልጽ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ነው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

ከዚህም ባለፈ ሀገራዊ የንግድ ፖሊሲው የተቀረጸው በኢትዮጵያ እየተገነባ ባለው የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ስርአት ማእቀፍ ውስጥ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ( ዶ/ር) የግሉን ዘርፍ ዋነኛ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር አድርጎ መውሰዱን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ የሀገሪቱን የንግድ ስርአት እንደመምራቱ መጠን ቀጣይ የንግድ ድርድሮችን፤ስምምነቶችንና ውህደቶችን አለምአቀፋዊ ተሞክሮዎችን እና የንግድ ሰንሰለት ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ሚኒስትሩ አክለው ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያም ከተሳታፊዎች የተሰጡ ግብአቶችን በቀጣይ እንደ ጠቃሚ ግብአት በመውሰድ ይፋ በሚደረገው የንግድ ፖሊሲ ውስጥ እንደሚካተቱ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ( ዶ/ር) በውይይቱ ማጠቃለያ መድረክ ላይ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ጠቃሚ የውይይት መድረክ ላይ የአዲስ ቻምበር የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እና ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በውይይቱ ላይ በመገኘት የንግዱን ማህበረሰብ ጥቅም ሊያስከብር የሚችልች የንግድ ፖሊሲ እንዲወጣ ግብአት ሰጥተዋል ።