የግብርና ምርት ውል/contract farming ቀደም ባሉት ግዜአት በሃገራችን በባህላዊ መንገድ የሚተገበር ሲሆን በዘመናዊ መልኩ በህግ ተደግፎ ተግባራዊ መሆኑ የምርት መጠንን ለመጨመር እንደሚያስችል የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ለባለድርሻዎች ባዘጋጀው ስልጠና ላይ ተጠቅሷል፡፡
ስልጠናው የአታክልት እና ፍራፍሬ ምርቶችን በስምምነትየግብርና ምርት ውል (Contract Farming) በመደገፍ ምርታማነታቸውን በመጨመር እረገድ ውጤታማነቱ እንዲሁም እንቅፋቶቹን የዳሰሰ ነው፡፡
የግብርና ምርት ውል/contract farming ጽንሰ ሃሳብን እና በሌሎች ሃገሮች ያለውን ተሞክሮ በማንሳት ስልጠናውን የሰጡት በማማከር ዘርፍ የተሰማሩት ዶ/ር በየነ ታደሰ ምንም እንኳ የስምምነት እርሻ ምርትን የመጨመር፡የአነስተኛ ገበሬዎችን ገቢ የማሳደግ ፡የአቅርቦት እሴት ሰንሰለትን ለማሻሻል፡የውጭ ንግድ መጠንን የማሳደግ፡የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ማድረግ እና የመበደር አቅምን የማሳደግ እድል የሚፈጥር ቢሆንም ዘርፉን ለመደገፍ የሚያስችል የብድር አቅርቦት ስላልተመቻቸለት እንቅፋት እንደሚገጥመው አንስተዋል፡፡
የግብርና ምርት ውል/contract farming የገንዘብ አቅም ባለው የግሉ ዘርፍ እና አምርቼ ማን ይገዛኛል የሚል ስጋት ባለበት ገበሬ መካከል በህግ ማእቀፍ በመደገፍ በጋራ የሚሰሩበት ሂደት ሲሆን ፡ከቅርብ ግዜ ወዲህ በተለያዩ የፍራፍሬ ምርቶች ውጤት እየታየበት መሆኑ ተነስቷል::
ከነዚህም አቮካዶ፡ፓፓያ እና ሙዝ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ለግብርና ምርት ውል/contract farming እንቅፋት ከሆነው የብድር አቅርቦት ባሻገር የመሰረተ ልማት አቅርቦት አለመሟላት፡ የገበሬዎች ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን የሚሉትም ተጠቅሰዋል፡፡
የግብርና ምርት ውል/contract farming ተግባራዊ ለማድረግ በገበሬዎች ዘንድ አሁን አሁን ፍላጎቶች እየታዩ ቢሆንም በገበያው ላይ የሚታየው የዋጋ መቀያየር ገበሬዎችን ደፍረው እንዳይገቡ እንቅፋት እየሆነባቸው መሆኑን ያነሱት ሌላው አሰልጣኝ ከግብርና ሚኒስቴር የመጡት አቶ ሱልጣን መሃመድ ሲሆኑ ለስምምነት እርሻ የወጣው አዋጅ መሰል ስጋቶችን መቅረፍ የሚችል እና ከምርት በኋላ ለሚኖር የዋጋ ልዩነት በስምምነት መሻሻል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
በስምምነት እርሻ ውስጥ የዋጋ፡ የአከፋፈል ሁኔታ፡ጥራትን፡መጠንን እና ቀንን የሚያካትት መሆኑ በአምራች እና በአስመራች መካከል በሚደረግ ህግን መሰረት ባደረገ ውል ጥራት ያለው ምርት እንዲመረት እና ከሃገር ውስጥ አልፎ የውጭ ገበያን የሚያሟላ ምርት ማምረት እንደሚያስችል ተጠቅሷል፡፡
በስልጠናው ማጠቃለያ እንደተጠቀሰው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የስምምነት እርሻ በሌሎች ሃገሮች ያስገኘውን ውጤት በሃገራችንም ለማየት የመንግስት ድጋፍ እና መተማመን አስፈላጊ ናቸውም ተብሏል፡፡