የካፒታል ገበያ የሚያስገኘውን እድል ለማሳካት ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ያስፈልጋል--የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት

የካፒታል ገበያ የሚያስገኘውን እድል ለማሳካት ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ያስፈልጋል–የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 25/2015 የካፒታል ገበያ ይዞ የሚመጣውን አዎንታዊ እድል ውጤታማ እንዲሆን መንግስት ጠንካራ ተቋማትን መገንባት እንደሚጠበቅበት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አመለከተ።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የካፒታል ገበያን አስመልክቶ ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት ውይይት በመካሄድ ላይ ነው።

በመድረኩ ላይም በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች በገበያው ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችላቸውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚኖርባቸው ገልጿል።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማጎልበት እና የምጣኔ ሀብትን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በግሉ ዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን ገንዘብ የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እና በስራቸው ላይ የሚያጋጥማቸውን ማነቆዎች በመቅረፍ በኩልም ያለው ሚና የጎላ ነው ብለዋል።

ይሁንና የካፒታል ገበያ ወደ ኢትዮጵያ ይዞ የሚመጣው አዎንታዊ እድል ስኬታማ እንዲሆን መንግስት ጠንካራ ተቋማትን መገንባት እና ባለሙያዎችን ማብቃት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ፕሬዝዳንቷ አስገነዝበዋል።

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ በበኩላቸው ተቋሙ የካፒታል ገበያን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ ድርጅቶች በምን መልኩ ወደ ካፒታል ገበያው ይቀላቀላሉ? የሚለውን አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችሉ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

የዛሬው ውይይት በካፒታል ገበያ ዙሪያ የባለድርሻ አካላትን ግብዓት መሰብሰብ አላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *