የካፒታል ገበያው በግሉ ዘርፍና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሚኖረው ሚና ዙሪያ ምክክር ተደረገ

ጥር 25/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ካፒታል ገበያው በግሉ ዘርፍና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሚኖረው ሚና ዙሪያ ምክክር እያደረገ ይገኛል።

ምክክሩን የአ.አ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ሰኪዩሪቲ ኤክስቼንጅ ተቋም በጋራ አዘጋጅተውታል።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መሰንበት ሽንቁጤ የካፒታል ገበያው ስርአት ለመጀመር የኩባንያዎች ጠንካራ አደረጃጀትና ግልጽ የፋይናንስ አሰራር ስርአት መከተል አለባቸው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቷ የካፒታል ገበያ ለመምራት የሚያስችል በቂ የሰው ሀይል አለመኖር በካፒታል ገበያ የሚሳተፉ በቂ የግልና የመንግስት ኩባንያዎች አለመኖር የገበያ ስርአቱ በኢትዮጵያ እንዳይጀመር አድርጎ ቆይቷል ብለዋል።

የካፒታል ገበያው መጀመሩ ቀጥተኛ ንግድ ለመሳብ የገንዘብ ፍሰትን ለማምጣት እና ዲያስፖራው ደህንነቱ የተጠበቀ ኢንቨስትመት ላይ እንዲሳተፍ እንደሚረዳም ተናግረዋል ፕሬዝዳንቷ።

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው የካፒታል ገበያውን በሀገሪቱ ለመጀመር ብቁ የባለስልጣን መስሪያ ቤት ማደራጀትና ወደ ገበያ የሚገቡ ድርጅቶች ተጠያቂነት ባለው መልኩ እንዲደራጁ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የካፒታል ገበያው ጠንካራ የፖሊሲ ማእቀፍ የሚያስፈልግ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ለወጤታማነቱ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እየሰራበት ይገኛል ብለዋል።

የካፒታል ገበያው የካፒታል እጥረት ያለባቸው ድርጅቶች ለኢንቨስትመንት የሚሆን ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያሰባስቡና አዲስ ኩባንያን ለማቋቋም እንደሚጠቅምም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያውን ለመጀመር የሚያስችል አዋጅ ከአንድ አመት በፊት መቋቋሙ የሚታወቅ ሲሆን ይህ የገበያ ስርአት ራሱን ችሎ የሚያስተዳድር የመንግስት ባለስልጣን የካፒታል ማርኬት ባለስልጣን ተብሎ መቋቋሙ ይታወቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *