የአዲስ ቻምበር አባል ኩባንያዎች በመድረኩ ላይ ከ340 ሚሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የንግድ ስምምነቶች መፈፀማቸው ተገልጿል ።
በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ተቋማት የቻይናን ትልቅ ገበያ “Big Market for All” እንዲጠቀሙም ጥሪ ቀርቧል።
(አዲስ ቻምበር ነሐሴ 13፣ 2018 አ.ም)
አዲስ ቻምበር ከቻይና ኤምባሲና የቻይና ንግድ ሚኒስቴር የንግድ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የቢዝነስ ለቢዝነስ መድረክ ላይ በርካታ የአዲስ ቻምበር አባል ኩባንያዎች መሪዎችና የሚመለከታቸው ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
በቻይና የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ቀዳሚ ትኩረት ከሚሰጣቸው አገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን የቻይና ንግድ ሚኒስቴር የውጭ ንግድ ዲፓርትመንት ም/ዋና ዳይሬክተር ቻንግ ሁይ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ላኪዎች ጥራት ያላቸውን ምርቶች ማቅረብና የተወዳዳሪነት ደረጃቸውን ጠብቀው መቀጠል እንዳለባቸውና የቻይና አስመጪዎች ጥራት ያላቸውን የኢትዮጵያ ምርቶችን በስፋት ለመግዛትና ዘላቂ የንግድ ድልድይ ለመገንባት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ይህንን የዜሮ ታሪፍ እድል ተጠቅመው በጥራትና በብዛት ተወዳዳሪ የሆነ ምርት በማቅረብ የድርጅቶቻቸውን እና የሀገሪቱን ገቢ ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።
ሰፊ ገበያ ለሁሉም በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የኢትዮ-ቻይና የቢዝነስ ለቢዝነስ (B2B) መድረክ ላይ የአዲስ ቻምበር ዋና ጸሐፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ መድረኩ ለንግድ ውይይት ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥ ላኪዎች ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያሻሽሉ፣ፈጠራን እንዲያሳድጉ እና ከቻይናውያን ሸሪኮቻቸው ጋር ልምድ እንዲለዋወጡ የሚረዳ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ በበኩላቸው፣ ሀገራቸው ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ህዝብ የሚገኝበት ሰፊ ገበያ እንዳላት ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ላኪዎች ከአለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች በመቋቋም ሰፊውን የቻይና ገበያ በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በቡና፣ በአኩሪ አተር፣ በቆዳና ሌጦ እንዲሁም በሰሊጥ ምርት ላይ የተሰማሩ ከ40 በላይ የአዲስ ቻምበር አባላትና የአገር ውስጥ ላኪዎች ከቻይና አቻዎቻቸው ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡
እነዚህ ስምምነቶች ከ340 ሚሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የንግድ ስምምነቶች እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ ቻምበር የግሉ ዘርፍ ድምጽ!
