የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ተወካይ አቶ ካሳሁን ሙላት ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተገኝተው ባሰተላለፉት መልዕክት ፤ እንደ አዲስ ቻምበር አይነት የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች በአዋጅ የተሰጣቸውን ተልዕኮ መሰረት መንግስትና በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ መካከል ድልድይ በመሆን የሚሰሯቸውን ስራዎች ከተማ አስተዳደሩ በበጎ ጎኑ ያያቸዋል ብለዋል ፡፡
አዲስ ቻምበር ዘመኑን የዋጅ አማራጭ የንግድ ፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ እና ችግሮችንም ሲከሰቱ የመፍትሄ አካል ሆኖ ፈተናዎችን ለመቅረብ ከንግድ ቢሮ ጋራ በጋራ መስራት አለብን ብለዋል፡፡
የግሉ ዘርፍ ሀብት እና እውቀት በመሰረተ ልማትና የአገልግሎት አቅርቦት ረገድ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከፍተኛ ሚና እንዳለው የንግድ ቢሮው ተወካይ አቶ ካሳሁን ገልፀዋል ፡፡
የከተማ አሰተዳደሩም ከግሉ ዘርፍ ጋር ለመስራት ቁርጠኝ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ካሳሁን ሁለቱ ወገኖች የጋራ ተጠቃሚነታቸው የሚረጋገጥበት መንገድ ማመቻቸት አስፈላጊ ነው ብለዋል ፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የጋራ ምክክር መድረክ እንዲኖር በማድረግ የንግዱ ህብረሰተብ በከተማዋ ከአዋጅ ፣ መመሪያ ፣ የአሰራር ሰርዓት ለመገንዘብ እንዲያስችለው እንዲሁም በግሉ ዘርፍ ዘንድ የሚፈጠሩ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማቅረብ ሰለሚያስችል አስተዳደሩ በትኩረት ያየዋል ብለዋል ፡፡
ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታ አማካሪ አቶ ግዛው ተክሌ በበኩላቸው ንግድ ምክር ቤቶች የግሉን ዘርፍ እድገት ለማስቀጠል የሚያከናውኗቸውን ስራዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በአዎንታዊ ጎኑ ይመለከታቸዋል ብለዋል ፡፡
ምክር ቤቱ ንግድን ለመስራት ያሉ ፈተናዎችን ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችውን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ በመስራት የሀገር ውስጥ ነጋዴዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
በአፍሪካ ቀጠናዊ ነፃ ገበያ በተፈጠሩና ሊፈጠሩ በሚችሉ አመቺ መልካም አጋጣሚዎች እና ዕድሎች ዙሪያ የግሉን ዘርፍ አስተዋፅኦ ለማጎልበት ከምክር ቤቱ ጋር አብረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል ፡፡
የአዲስ ቻምበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሽንቁጤ ምክር ቤታቸው እያደገ ከመጣው የንግዱ ማኅበረሰብ ፍላጎት ጋር አብረው የሚሄዱ አገልግሎቶች ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎችን መሰራቱን ገልፀዋል ፡፡
የዳይሬክተሮች ኢንስቲትዩት እና የቢዝነስ ማበልጸጊያ/ ኢኖቬሽን/ ማዕከል በ2015 በይፋ ሥራ እንዲጀመሩ መደረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል ፡፡
አክለውም የዳይሬክተሮች ኢንስቲትዩት የኩባንያዎችን ዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትና አመራሮችን በኩባንያ መልካም አስተዳደር እና በአመራር ረገድ አቅም እንዲገነባ ሆኖ የተቀረፀ ነው ብለዋል ፡፡
ይህም በሀገሪቱ ያለውን የኩባንያ አመራር ክፍተት በመሙላት ረገድ ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን አመልክተዋል ፡፡
ምክር ቤታቸው የቢዝነስ ማበልጸጊያ/ኢኖቬሽን/ ማእከል ፕሮጀክት ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉን ለጉባኤው ገልፀዋል ፡፡
የቢዝነስ ማበልጸጊያ ማዕከሉ በአዲስ አበባ የሚገኙ ወጣት እና ጀማሪ የስራ ፈጣሪዎችን የሚደግፍ ፕሮጀክት እንዲሆን የተቀረፀ መሆኑንም ተናግረዋል ፡፡
የንግዱን ህብረተሰብ ችግሮች፤ጥያቄዎችና አንገብጋቢ ጉዳዮች ለመንግሥት በማቅረብ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለማድረግ የምክር ቤታቸው የአድቮኬሲ ሥራዎችን እየተሰራ መሆኑን ወ/ሮ መሰንበት ተናግረዋል ፡፡
በጉባኤው የ2015 ዓ.ም ሪፖረት ፤ በውጭ የአዲት የቀረበለትን የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ከተወያየ በኃላ በማፀደቅ ተጠናቋል ፡፡