በናይሮቢ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ አምባሳደር ወርቃለማሁ ደስታ በአገራችን የInstitute of Directors (IoD) ለማቋቋም እንዲረዳው በናይሮቢ የልምድ ልውውጥ እያደረገ ከሚገኘው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት የልዑካን ቡድን ተቀብለው ኖቬምበር 3 ቀን 2022 ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ ወቅት የምክር ቤቱ ዋና ጸሃፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በአገራችን የInstitute of Directors (IoD) ለማቋቋም የሚረዳውን የጉድኝትና ትብብር ስምምነት ከKenya Institute of Directors (IoD) ጋር በእለቱ መፈራረማቸውን ገልጸዋል።
አክለውም በአገራችን የInstitute of Directors (IoD) መቋቋም በተለያዩ የግል ኩባንዎችና የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ የቦርድ ዳይሬክተሮች የኮርፖሬት አስተዳደርን ሀሳቦችንና አላማዎችን ለየኩባንያዎቻቸው በማስተዋወቅ ስራቸውን አለም አቀፍ ስታንዳርድን በጠበቀ መልኩ ሙያዊ ስነ ምግባርን ተከትለው ለኩባንያቸው ትርፋማነት በተጠያቂነት መንፈስ በሃላፊነትና በትጋት የመስራት ባህልን እንዲያዳብሩ እንደሚረዳቸው ዋና ስራ አስፈጻሚው አስረድተዋል።
የንግድ ማህበሩ የአገራችን የግሉ ሴክተር ለአገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያደረገ ያለውን ቁልፍ አስተዋጽኦ አድንቀው ምክትል አምባሳደሩ በአገራችን የInstitute of Directors (IoD) መቋቋም እንዲሳካ ሚሲዮኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በውይይቱ በአገራችንና በኬንያ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግና ለማበረታታት በጋራ የተለያዩ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ፎረሞችን ለማካሄድ፣ የተጀመሩ ቀጠናዊ ትስስሮችን ለማጠናከር፣ ተገቢ መረጃዎችን ለመለዋወጥና ከንግድ ጋር በተያያዘ በሁለቱ አገራት መካከል የሚፈጠሩ ተግዳሮቶችን ለመፈታት ተባብሮ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል።
የልኡካን ቡድኑ ከኦክቶበር 30-ኖቬምበር 5 ቀን 2022 ዓ.ም በኬንያ በሚኖረው የልምድ ልውውጥ ቆይታ በኬንያ በንግዱ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱ ታዋቂ የንግድ ማህበራትና እና ባለሃብቶችን አግኝተው ውይይት እንደሚያደርጉ ለማወቅ ተችሏል።