በስራ አጥነት ምክንያት ሊመጣ የሚችልን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮት ለመታደግ የበኩሉን እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት/ አዲስ ቻምበር/ አስታወቀ፡፡
ይህንን ያሉት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሀፊ አቶ ሺበሺ ቤተ ማርያም የአዲስ ቻምበር የቢዝነስ ኢንኩቤሽን/ የቢዝነስ ማበልጸጊያ/ ማዕከል ለስራ ፈጣዎች ያዘጋጀውን ሰልጠና በከፍተቱበት ወቅት ነው ፡፡
በኢትዮጵያ እድሚያቸው ከ19 እስከ 25 የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛውን ቁጥር መያዛቸው እድልም ፈተናም ነው ያሉት አቶ ሺበሺ ወጣቱ ስራ እንዲፈጥር ልንደግፈው ይገባል ብለዋል::
በየአመቱ ከመንግስትና ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ተመርቀው እንደሚወጡ ጠቁመው ወጣቱ ስራ እንዲፈጠር እና ወደ ቢዝነስ እንዲገባ ልንደግፈው ይገባል ብለዋል ፡፡
ይህንን በማድረግ በስራ አጥነት ምክንያት ሊመጣ የሚችልን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፈተና እንደንግድ ምክር ቤት ልንታደገው እንችላለለን ያሉት አቶ ሺበሺ ፤ አዲስቻምበር ከአውሮፓ ህብረት ባገኝው የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት የቢዝነስ ኢንኩቤሽን ማዕከል አቋቁሞ ስራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ እየሰራ ይገኛል ብለዋል ፡፡
የቢዝነስ ማበልጸጊያ ማዕከሉ የፕሮጀክት ስራ አሰኪያጅ አቶ አማኑኤል ለማ በበኩላቸው ማዕከሉ በዋናነት ወጣትና ጀማሪ የስራ ፈጣሪዎችን የሚደግፍ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው እንዲህ አይነት ፕሮጀክቶች ሀገርን የመለወጥ አቅም አላቸው ብለዋል፡፡
አቶ አማኑኤል አክሎም 90 በመቶ የሚሆኑት ስራ ፈጣሪዎች አምስት አመት ሳይሆናቸው የሚከስሙ መሆናቸውን ገልጸው ፤ ይህ የሚሆነው ወድቆ የመነሳት ልምድ ባለመኖሩ ነው ብለዋል፡፡ ፡፡
የቢዝነሰ ማበልጸጊያ ማዕከሉ ስራ ፈጣዎች ለመደገፍ ሰልጠናዎችን ጀማሪ እና በስራ ላይ ላሉ በሚል በሁለት ከፍሎ እንደሚሰጥ የፕሮጀክት ስራአስኪያጁ ለአዲስ ቻምበር ሚዲያ ገልፀዋል ፡፡
ለጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች የክህሎት ስልጠና ከመሰጠት ባሻገር የስራ ማሰጀመሪያ ገንዘብ ወይም ሲድ መኒ የሚያገኙ ሲሆን ፤ በዚህም በመጀመሪያ ዙር ከ 10 ድርጅቶች ለተውጣጡ 20 ስራ ፈጣሪዎች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ስራ ላይ ላሉና የቢዝነስ ሃሳብ ድጋፍ ለሚፈለጉ ደግሞ ሰልጠናው እስከ አራት ወራት ድረስ የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው አብዛኛው ስራ በተግባር ስራ ላይ ሆነው የሚሰጣቸው መሆኑን ሰምተናል፡፡ ፡፡
ቢክ ኢትዮጵያ አዲስ ቻምበር ከአውሮፓ ህብረት ባገኝው የገንዘብ ድጋፍ የተቋቋመ ፕሮጀክት ሲሆን ለአራት አመት ለስራ ፈጣሪዎች ድጋፍ የሚያደርግ ፕሮጀክት መሆኑን በፕሮግራሙ ላይ ተገልጿል ፡፡