የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጠንካራና ተወዳዳሪ የግል ዘርፍ እንዲፈጠር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ምክር ቤቱ አመቺ የሆኑ ንግድ ነክ ፖሊሲዎችና ህጎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ለመንግስት የፖሊሲ ግብአትን በመስጠት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡
በተለይም ምክር ቤቱ የበጎፍቃድ አምባሳደሮችንና የተለያዩ የአድቮኬሲ ኮሚቴዎችን በመሰየም እና በጠንካራ የስትራቴጂክ አመራር በመታገዝ ዘላቂ የሆነ የንግድ ምክር ቤት እንዲፈጠር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ይህን እንቅስቃሴ በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለውን የምክክር መድረክ በቅርቡ ከተመረጡ የምክር ቤቱ በጎ ፍቃድ አምባሳደሮች ጋር አካሂዳል፡፡
በኢንተርሌግዠሪ ሆቴል በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የምክር ቤቱ የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮች ንግድ ምክር ቤታቸውን በቅንነትና በትጋት ለማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የምክር ቤቱ የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮች በቢዝነስና ንግድ አመራር የበርካታ አመታት ልምድ ያላቸው መሆኑ የምክር ቤቱን ተደራሽነት ከፍ ለማድረግ እና የምክር ቤቱን ስትራቴጂክ ግቦች ለማሳካት አይነተኛ ሚና እንዳለው የምክር ቤቱ ፕረዚደንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ምክር ቤቱ የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮች ቢኖሩትም በተለያዩ ምክንያቶች መጠቀም እንዳልተቻለ ፕረዚዳንቷ አክለው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የቻምበር የቦርድ አባላት በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩ አሁንም ባላቸው አቅምና ጊዜ ምክር ቤቱን ማገልገል እንደሚገባቸው በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡
በዚህ የምክር መድረክ ላይ ጠንካራና ቁርጠኛ የሆኑ የቻምበር የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮችን እውቀትና አቅምን ስልታዊ በሆነ መልኩ እንዴት መጠቀም ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮችን ቁጥር የመወሰን አስፈላጊነት ላይ ፤የአገልግሎት ዘመን ወሰን፤ የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮች ተጽእኖ እንዲኖቸው ማስቻል፤ ከመንግስት ጋር የሚደረጉ የምክክር መድረኮች ላይ የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮችን ሚና የማሳደግ አስፈላጊነት ላይ እንዲሁም መንግስት፤መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የሸማች ማህበራት የቻምበር የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮች እንዲሆኑ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
ከዚህም ባለፈ የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮች ቀጣይነት ያለው የውይይት መድረክ እንዲፈጥሩና ተቋማዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ ሀሳብ ተሰንዝራል፡፡
በሪፎርም ሂደት ላይ የሚገኘው ምክር ቤት በባለፈው አመት 75ኛ አመቱን ያከበረ ሲሆን ለምክር ቤቱ አስተዋጾ ላደረጉ አካላት ምስጋናና እውቅና መስጠቱ የምክር ቤቱን የበጎ ፍቃድ አገልጋዮችን ቁርጠኝነት ከፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
ከዚህም ባለፈ የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮች ምክር ቤቱ የሚያስገነባውን የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ግንባታ ፕሮጀክትን ባላቸው አቅምና ጊዜ እንዲደግፉ ጥሪ ቀርቧል፡፡ ከምክር ቤቱ ህንጻ ግንባታ ጋር በተያያዘ ምክር ቤቱ አሁን ያለውን የግንባታ ግብአት ዋጋ ከግምት ውስጥ ያስገባ የዋጋ ክለሳ ማድረግ እንዳለበት፤ከአባላት መዋጮ ባለፈ እንደ አክሲዮን የመሳሰሉ ሌሎች የፋይናንስ ምንጮችን መፈለግ እና የሌሎች ውጤታማ ተቋማት የህንጻ ፕሮጀክት ተሞክሮዎችን መውሰድ እንዳለበት ምክረሀሳብ ቀርቧል፡፡
ከዚህ ቀደም በአመራር ቁርጠኝነት ማነስ ምክንያት የህንጻ ግንባታ እንቅስቃሴ እንዳላረገ የተገለጸ ሲሆን አሁን ላይ ግን የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮችን በመጠቀም እና የፕሮጀክት ትግበራ ስትራቴጂን በመንደፍ ፤ ያለምንም ወጪ የህንጻ ዲዛይን መስራት እንደተቻለ፤ ከአበዳሪ ተቋማት ጋር ንግግር እንደተጀመረ እና እንቅስቃሴዎች እንደተጀመሩ በውይይት መድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡
በመጨረሻም የቻምበር የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮች ሰብሳቢ፤ ምክትል ሰብሳቢና ጸሀፊን በመምረጥ ውይይቱ አብቅቷል፡፡