አዲሱ አገልግሎት የንግዱ ሕ/ሰብ ብድር ለማግኘት ያለበትን የቆየ ችግር ይቀርፋል ተብሏል፡፡
በይድነቃቸው ዓለማየሁ
የክሬዲት ሬቲንግ አገልግሎት በዓለም ላይ የተለመደ አሰራር ሲሆን አገልግሎቱም የቢዝነስ ኩባንያዎች ለብድር ብቁ መሆናቸውን በተቀመጡ መመዘኛዎች አማካኝነት በማጣራት እና ሰርተው ብድር የመመለስ ብቃት አንዳላቸው ለአበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት ማረጋገጫ በመስጠት ነጋዴዎች የብድር አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኙ ይረዳል ተብሏል፡፡
ይህን አዲስ አገልግሎት ለማስተዋወቅ በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የንግድ ም/ቤቱ ፕሬዝደንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ብድር ማግኘት ከፍተኛ ውጣ ውረድ የሚጠይቅ እና ለአመታት የነጋዴው ዋነኛ የዕድገት ማነቆ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል፡፡
ታዲያ ንግድ ምክር ቤቱ ያስተዋወቀው ይኸው አገልግሎት ለንግዱ ሕብረተሰብ የክሬዲት ሬቲንግ አገልግሎት በመስጠት ነጋዴው ያለበትን የብድር የማግኘት ችግር ለመቅረፍ ያስችላል ብለዋል፡፡
የክሬዲት ሬቲንግ አገልግሎት በአበደሪ ባንኮች እና በተበዳሪ ኩባንያዎች መካከል መተማመን እና ዘላቂ ትብብር እንዲኖራቸው ትልቅ ድርሻ አለው ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የአዲስ ቻምበር ዋና ጸሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በበኩላቸው ንግድ ምክር ቤቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘመኑ የሚጠይቀውን አዳዲስ አገልግሎቶችን ለንግዱ ሕብረተሰብ ማቅረብ መጀመሩን ገልጸው፤ የዳይሬክተሮች ተቋም እና የጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ለአባላቱ እና ለመላው የንግድ ሕብረተሰብ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ በተለይ አዲሱን የክሬዲት ሬቲንግ አገልግሎት ከድርሻ ገበያ ጋር ተያይዞ ለአባላቱ ለመጀመር ተቀማጭነቱ ዱባይ ከሆነው ኢንተርናሽናል ክሬዲት ሬቲንግ አጀንሲ (ICRA) ጋር በትብብር ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ ቀደም ሲል መፈራረሙን ገልጸዋል፡፡
መንግስት የጀመረውን የፋይናንስ ሪፎርም ተከትለው የተቋቋሙት እንደ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን እና የሴኪዩሪቲ ኤክስቼንግ ያሉ መስሪያ ቤቶች ተልዕኮአቸውን ማስፈጸም የሚችሉት የክሬዲት ሬቲንግ አገልግሎት ሰጪ ተቋም መኖር ሲችል ነው ብለዋል፡፡
ስለዚህ አዲስ ቻምበር ተነሳሽነቱን አስቀድሞ ጀምሯል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ የንግዱን ሕብረተሰብ አቅም በመገንባት ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆን ቤቱ ዘመኑ የሚጠይቀውን አገልግሎት ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ስለ ክሬዲት ሬቲንግ አገልግሎት ፅንሰሃሳብ፤መርሆች፤ የአተገባበር ስልቶች እና የአገራት ተሞክሮዎች በተለያዩ ምሑራን ገለጻ ተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡