የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከዳኒሽ ኢንዱስትሪ ኮንፌዴሬሽን (DI)ጋር በመተባበር በግብርና ምርት ማቀነባበር ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ አምራቾች እና ላኪዎች በሴቶች እኩል ተሳታፊነት እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ በማህበራዊ እና የድርጅት መልካም አስተዳደር ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ሴቶች ዘርፈ ብዙ በሆኑ ችግሮች ምክንያት ተጠቃሚ ከሚሆኑባቸው እድሎች ወደኋላ እንደሚቀሩ የተጠቀሰ ሲሆን ከዚህም በስራ ቦታዎች ለሴቶች ምቹ የሆነ፡ተጠቃሚ እንዲሁም ደህንነታቸውን ለመጠበቅ የሚያግዛቸው ፖሊሲዎች በበቂ አለመኖራቸው እንዱ ችግር መሆኑ ተጠቅሷል ::
የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት አስመልክቶ በሃገራችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያስረዱት አሰልጣኝ አስቴር አስፋው፡ሃገራችን ከቅርብ ግዜ ወዲህ የሴቶችን ተሳታፊነት የሚያጠናክሩ ህጎች እየተሻሻሉ የመጡ ቢሆንም አሁንም ተጨማሪ ስራዎችን የሚጠይቁ መሆናቸውን ገልጸዋል::
ለዚህም በተለያዩ የአመራር ቦታዎች ላይ የሴቶች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ መገለጫው መሆኑን አንስተዋል፡፡
በየሃገራቱ የማህበራዊ እና የአኗኗር ልዩነት ቢኖርም በሴቶች እኩል ተጠቃሚነት ላይ ያሉ እንቅፋቶች የመመሳሰል እድል እንዳላቸው የዳኒሽ ኢንዱስትሪን (DI) ተሞክሮ ሲያጋሩ ያነሱት ክላራ ሃልቮርሰን የዳኒሽ ኢንዱስትሪ ኮንፌዴሬሽን ከፍተኛ አማካሪ ያነሱ ሲሆን በዴንማርክ የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት ለማሳካት እንዲሁም በአመራር ቦታ ላይ ያሉ ልዩነቶችን ለማጥበብ በተቋማት ፖሊሲዎች እንደሚደገፍ ገልጸዋል፡፡
በድርጅቶች ውስጥ ሴቶችን ለስራ የሚጋብዙ እና የሚያሳትፉ እንዲሁም ደህንነነታቸውን ማስጠበቅ የሚቻልባቸው በፖሊሲ የተደገፉ አሰራሮች መኖር፡ሴቶች በተፈጠረላቸው የስራ እድል በሰፊው የመሳተፍ እና የስራ ቦታቸው ከአደጋ የጸዳ እንዲሆን እንደሚያደርገውም ተጠቅሷል::
በዚህም በስራ ቦታቸው የሚደርስባቸውን ጾታዊ ጥቃት ለመቀነስና ብሎም ለማስቀረት ድርጅቶች ጥቃቱን መከላከል የሚያስችል አሰራር ሊኖራቸው ይገባል ተብሏል፡፡
በስልጠናው የተሳተፉ አምራቾችም በድርጅቶቻቸው ውስጥ ሴቶችን ማእከል ያደረጉ ልምዶቻቸውን ያካፈሉ ሲሆን በቀጣይም የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል እና ደህንነቶቻቸውን የሚያስጠብቅ ፖሊሲ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡