አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ለመመለስና በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ ድጋፍና ትብብር ወሳኝ መሆኑን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ገለጹ።
በዚሁ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ለመመለስና በዘላቂነት ለማቋቋም ከመንግሥት ጥረት ባለፈ የግሉ ዘርፍ ድጋፍና ትብብር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በኮሚሽኑ በኩል የቀድሞ ታጣቂዎችን በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በመጥቀስ ለስኬታማነቱ የሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ለኮሚሽኑ ጥረት መሳካት በተለይም የንግዱ ማኅበረሰብ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው÷ በተቻለ አቅም ሁሉ የፋይናንስና የዓይነት ድጋፎችን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው÷ የሰላም እጦት በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ በመሆኑ ለዘላቂ ሰላም መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በመሆኑም ምክር ቤቱ ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር እንደሚሠራ አረጋግጠው÷ የሰላምና የመልሶ ግንባታ ጉዳይ የጋራ አጀንዳችን ሆኖ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡