የሀገር ውስጥ የባንክ ዘርፍ ለውጪ ባንኮች መከፈት እድልና ተግዳሮቱ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ከመፈቀዱ ጋር ተያይዞ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ባለሙያዎች ፖሊሲው ከመተግበሩ በፊት ዳግም በእድሎቹና ተግዳሮት ዙሪያ መፈተሽ ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ፖሊሲውን ለመተግበር የወጡ ረቂቅ መመርያዎችን ተከትሎ በጉዳዩ ላይ በተዘጋጁ የውይይት መድረኮች ላይ የውጭ ባንኮች አገባብ ላይ መንግሥት ጥንቃቄ ያድርግ የሚባለው ግፊት እየጨመረ መምጣቱንም ለመረዳት ተችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበር ምክር ቤት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ እንደተናገሩት ባለፉት በርካታ አስርት አመታት ሀገራችን በሯን ለውጭ የፋይናንስ ተቋማት ዝግ ማድረጓን ገልጸው ንግድ ምክር ቤታቸው የውጪ ባንኮች በሀገራችን የባንክ ዘርፍ ቢሳተፉ ከሚኖር ተግዳሮት ጎን ለጎን የሚገኙ እድሎችም እንዳሉ እንረዳለን ብለዋል፡፡

በተለይ ‹‹የግል ባንኮች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?፣ የሚኖረው የውድድር አውድ እስከምን ድረስ ነው? የሚለው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ይህንን ዕርምጃ ዕውን ማድረጉ ምን ጥቅም ያስገኛል? ምንስ ያሳጣል? የሚለው የአባሎቻችንም ሆነ የንግድ ምክርቤታችን ጥያቄ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በእርግጥ የውጭ ባንኮች በሀገራችን መግባታቸው ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጥርጥር ባይኖርም አገባባቸው ግን የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ይህም አጠቃላይ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ከማሳደግና ለአገር ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር ታይቶ የሚወሰድ ዕርምጃ ይሆናል ብለንም እንገምታለን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በፓናሉ ተናጋሪ ከነበሩት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች መካከል ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው እንደገለጹት ከውጭ ባንኮች መግባት ጋር በተያያዘ ሦስት ዋና ዋና ተግዳሮቶች ይገጥማሉ፡፡

ሊገጥሙ የሚችሉት ችግሮች የማክሮ ፋይናንስ መዛባት፣ በባንኮቹ ውስጥ ያለው ችግርና ከብሔራዊ ባንክ አቅም ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ጠቁመው፣ እንዲህ ያሉ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ የውጭ ባንኮችን ማስገባት ከባድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የውጭ ባንኮች መግባት ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም የተለያዩ ጥናቶች የሚያመለክቱ ግን የሚባለውን ያህል ጥቅም የሚያመጣ አለመሆኑንና በተለይ የማክሮ ኢኮኖሚው ባልተረጋጋበት ሁኔታ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የሚፈቅደውን ፖሊሲ መተግበር ጉዳት ያመጣል የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

ከማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ጋር የተያያዙት የዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ጦርነት የኢኮኖሚ ውጥኑን ለማስፈጸም ፈታኝ እንደሚሆኑም ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል፡፡

በዚህ መድረክ ላይ ሌላው ማብራሪያ የሰጡት የአሐዱ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፋንታዬ፣ አሁን ባለው ሁኔታ የውጭ ባንኮች ይግቡ ማለት ብዙ ችግሮች ያስከትላል የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

በተለይ ለዓመታት የገንዘብ ፖሊሲው ችግር ያለበት ሆኖ ከመቆየቱ አንፃር የውጭ ባንኮችን ማስገባት መፍትሔ እንደማይሆንም ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ባንኮች መግባት የለባቸውም የሚል እምነት እንደሌላቸው ያመለከቱት አቶ እሸቱ ነገር ግን አሁን እንዲገቡ የሚፈለግበት መንገድ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል ብለዋል፡፡

ይህ ፖሊሲ ወደ 500 ሺሕ የተጠጉ የባንክ የአክሲዮን ባለቤቶችን መብት ሊያስጠብቅ መቻል እንዳለበትም በመጠቆም የውጭ ባንኮች ጥቅም ይሰጣሉ ብቻ ሳይሆን ጉዳት የሚያስከትሉ መሆኑ መታሰብ ስላለበት ፖሊሲውን ለመተግበር ሥጋትን የሚቀንሱ መመርያዎች የሚያስፈልጉ መሆኑን ነው፡፡

እንደ አቶ እሸቱ እምነት የሚገቡት ባንኮች ለምሳሌ የኤክስፖርት ሥራ እንዲሠሩ መፈቀድ የለበትም፡፡ ምክንያቱም ባንኮች እየሠሩት ስለሆነ ይኼ ሥራ ከውጭ ባንኮች ከሥራ ዝርዝር ውስጥ መካተት እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ እሸቱ ምልከታ የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲከፈቱ አገር ውስጥ ሊያበድሩ የሚችሉትን ሀብት ማምጣት ያለባቸው መሆኑን ነው፡፡ በአገር ውስጥ ሀብት መጠቀም እንደሌለባቸው አመልክተዋል፡፡

የአገር ውስጥ ሀብትን ሰብስበው የሚያበድሩ ከሆነና በዚህ ሥራቸው በጣም ውጤታማ መሆን ቢችሉ እንኳን እንደ አገር የመጨረሻው ውጤት አገርን መጉዳት ነው ይላሉ፡፡

ስለዚህ እነዚህ ባንኮች የራሳችንን ሀብት ለብድር ማቅረብ አግባብ ስለማይሆን ይግቡ ከተባሉ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ሁሉ መታሰብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የባንኮቹ አከፋፈት ምን መሆን እንዳለበት በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ በቅደም ተከተል መተግበር የሚኖርበት መሆን እንዳለበት ያምናሉ፡፡

በየትኛውም መንገድ ቢገቡ ተቀማጭ ገንዘብ የማይወስዱና የውጭ ምንዛሪ ሥራዎች ላይ እንዲሠሩ የማይፈቀድላቸው መሆን አለበት፡፡

በአብዛኛው የገቢ ምርቶች ላይ የውጭ ምንዛሪ ማምጣታቸው ላይ ያተኮረ የባንክ ሥራ እንዲሠሩ ተደርጎ መመርያዎች መቀረፅ ይኖርባቸዋል የሚል ምክረ ሐሳብም ሰንዝረዋል፡፡

የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ የእነዚህ ባንኮች መግባት ጠቃሚ ጎን ያላቸው መሆኑን አስረድተው ሊያሳርፉ የሚችሉት ተፅዕኖ ግን በጥንቃቄ መታየት ይኖርበታል፡፡

ከዚህ ውጭ ግን አሁን የመንግሥት አቋም የሚያሳየው መግባታቸው የማይቀር በመሆኑ ‹‹ይግቡ አይግቡ›› የሚለው ጉዳይ ያበቃለት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳቱን ቀንሶ እንዴት ገብተው መሥራት እንደሚኖርባቸው በመነጋገርና እንዲህ ባሉ መድረኮች ላይ እየቀረቡ ያሉ ሐሳቦችን ብሔራዊ ባንክ በመመርያዎቹ እንዲያካትት መግፋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ባንኮች መግባታቸው አይቀርም ብለን ስንዘጋጅ ቆይተናል ያሉት የህብረት ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ከበደ በበኩላቸው ነገር ግን አገባቡ ደረጃ በደረጃ መግባት ያለባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ መላኩ የባንኮቹ አገባብ መጀመርያ በሽርክና (በፓርትነርሺፕ) ቢጀመር ጠቃሚ እንደሚሆን ገልጸው፣ ከዚህ ልምድ በመነሳት ወደ ሌሎቹ አማራጮች መግባት ይቻላል ብለዋል፡፡ ሁሉንም አማራጮች በአንዴ መጠቀሙ ግን ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ፖሊሲው አይፈጸም የሚል ፍላጎት እንደሌላቸው የገለጹት አቶ እሸቱ ደግሞ ባለአክሲዮኖቻችን እንዳይጎዱ የውጭ ባንኮች አገባብ ደረጃ በደረጃ መሆን አለበት ይላሉ፡፡

እንደ ህንድና ሲሪላንካ ያሉ አገሮችም የውጭ ባንኮችን ያስገቡት ደረጃ በደረጃ በመሆኑ በፖሊሲ ስህተት አገርም ባንኮችን የፈጠሩ ባአክሲዮኖችም እንዳይጎዱ የውጭ ባንኮች አገባብ ደረጃ በደረጃ ሊሆን የሚገባ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ይህንን ሐሳብ የዕለቱ ተናጋሪዎች ሁሉም የተጋሩት ነበር፡፡

በዕለቱ ከተናጋሪዎቹም ሆነ ከተሳታፊዎቹ የተሰጡ በርካታ አስተያየቶች የተነሱ መሆናቸውን የገለጹት ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) ይህ የሚያሳየው ፖሊሲው ሲወጣ ከኋላ ባዶ እንደሆነ ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ የቀረቡትን ሐሳቦች ግብዓት አድርጎ መንግሥት እንዲጠቀምበት ማደረግ ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የሕግ ባለሙያው ፈቃዱ ጴጥሮስ (ረዳት ፕሮፌሰር) ደግሞ ከሕግ አንፃር መታየት አለባቸው ያሉዋቸውን ሐሳቦች አቅርበዋል፡፡

በተለይ ለውጭ ባንኮች እስከ 30 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ እንዲሰጣቸው በረቂቅ ሕጉ ላይ የተቀመጠው አንቀፅ ለኢትዮጵያውያኖችም ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡ እስካሁን ያለው ሕግ አምስት በመቶ ብቻ የሚፈቅድ በመሆኑ ይህ ሕግ መስተካከል አለበት ብልዋል፡፡

ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ያሬድ ኃይለ መስቀል ደግሞ የውጭ ባንኮች መግባት ተግዳሮት ያለው ቢሆንም ገብተው እንዲሠሩ መፈቀዱ አግባብ እንደሆነና የኢትዮጵያ ባንኮችም ለዚህ ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡

የፓናል ውይይቱን የአዲስ ቻምበር ዋና ጸሃፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም የመሩት ሲሆን ንግድ ምክር ቤቱ ይህንን እና መሰል ጉዳዮችን ለፖሊሲ አውጪዎች እንደሚያቀርብ እና ለአድቮኬሲ እንደሚያውለው ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *