መርሃግብሩ (ፕሮጀክቱ) በዋነኛነት በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ረዳት ያጡትን ዜጎችንና ዝቅተኛ ደሞዝ ያላቸውን የኩባንያ ሰራተኞችን ታሳቢ አድርጎ የሚደግፍ ነው፡፡
ያልበሰሉ ምግቦችን ለ2 ወራት ከ15 ሺኅ እስከ 20 ሺ የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን ለማይችሉ ዜጎች ማከፋፈል አንዱ የፕሮጀክቱ አካል ሲሆን፣ ለዚህ የፕሮጀክት ክፍል 16 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የበጀት ግምት እንደተቀመጠለት ሐሙስ፣ ሐምሌ 14፣ 2014 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል በተካሄደ የመርሃ ግብሩ ማስተዋወቂያና ቃል ኪዳን መግቢያ ዝግጅት ወቅት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ ሽበሺ ቤተማርያም ለንግድ ምክር ቤቱ አባላት ገለፃ አድርገዋል፡፡
ሌላው የዚሁ ፕሮጀክት መርሃግብር አካል የበሰሉ ምግቦችን የምሳ አቅርቦት ሲሆን፣ በዚህም ከ16 ሺ 800 እስከ 24 ሺ ግለሰቦችን ምሳ ማብላትን ያካትታል፡፡ ለዚህም 1.4 ሚሊዮን ብር የበጀት ግምት ተተምኗል፡፡
ሶስተኛው የፕሮጀክቱ አካል ዝቅተኛ ክፍያ ላላቸው የኩባንያ ሰራተኞች ቀለብ ማቅረብ ነው፡፡ በዚህም በ100 ድርጅቶች ውስጥ ያሉ 4 ሺ አባወራዎች ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ለሰራተኞቹ የሚመደበው ወጪም እንደሰራተኞቹ ብዛትና በሚከፈላቸው ደሞዝ መጠን ይወሰናል፡፡
ፕሮጀክቱ ከዚህ በተጨማሪም የንግድ ምክር ቤቱን አባላትና የኩባንያ ኃላፊዎችን በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብር ላይ ማሳተፍንም ይጨምራል፡፡
ጠቅላላ የፕሮጀክቱ ወጪ 20 ሚሊዮን ብር መሆኑም ተገልጿል፡፡
አዲስ አበባ 25 በመቶ የሚኖሩ ዜጎቿ ከድህነት ወለል በታች ህይወትን ይገፋሉ፡፡
በፕሮጀክቱ ማስተዋወቂያ መድረክ ላይ የተገኙት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር አባይ በአዲስ አበባ ትልቁ ክፍት ገበያ (Open Market) የሆነውና ከፍተኛ የፋይናንስ ዝውውር በሚካሄድበት መርካቶ በሚገኝበት አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እንደአብነት በመጥቀስ፣ በሥፋራው ምግብና የመኖሪያ ቤት የሚቸግራቸው በርካታ ዜጎች እንዳሉ አንስተዋል፡፡
በከተማዋ ያሉ ችግረኞችን ለመርዳትም ባለሃብቶችን ጨምሮ ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ ያነሱት ምክትል ከንቲባው፣ የከተማ አስተዳደሩ በሚያከናውነው የትምህርት ቤት ምገባ (School Feeding) መርሃ ግብር ውስጥ 600 ሺ ተማሪዎችን እየመገበ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው ምክር ቤታቸው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ረዳት የሌላቸውን ዜጎች ለማገዝ 6.2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የንግድ ምክር ቤቱ አባላት የበጎ አድራጎቱ ድጋፍ አድራጊዎች እያንዳንዳቸው ከ200 ሺኅ እስከ 700 ሺህ ድጋፍ ለማድረግ በድጋፍ ማድረጊያ ቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ ቃል እንደሚገቡም ተስፋ ተጥሏል፡፡ የድጋፍ አይነቶቹም ከገንዘብ ባሻገር በአይነትና በተለያዩ መንገዶች ማድረግ እንደሚቻል ተገልጿል፡፡ (ኢትዮ የንግድና ኢንቨስትመንት መድረክ)