አዲስ ቻምበር “የሥራ መሪዎች መድረክ” አገልግሎትን በይፋ ጀመረ

አዲስ ቻምበር “የሥራ መሪዎች መድረክ” አገልግሎትን በይፋ ጀመረ
በይድነቃቸው ዓለማየሁ
“የሥራ መሪዎች መድረክ” የተሰኘው ንግድ ም/ቤቱ ያስ ጀመረው አገልግሎት አንጋፋ የቢዝነስ መሪዎች ዕውቀታቸውን እና ያለፉበትን ልምዳቸውን ለዛሬዎቹ ተተኪ ወጣት መሪዎች የሚያካፍሉበት የመማማሪያ መድረክ ነው፡፡
በሥነሥርዓቱ ላይ የአዲስ ቻምበር ፕሬዝደንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የመሪነት ሚና ለአንድ ተቋም ውድቀትም ይሁን ስኬት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡
መድረኩ ወጣት የቢዝነስ ሥራ መሪዎችን አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡ መድረኩ አባት እና እናት መሪዎች ፈተናዎችን በየጊዜው እየተጋፈጡ እንዴት በብልሃት አልፈው የሚመሩትን የቢዝነስ ተቋም ከውድቀት ወደ ስኬት እንዳሻገሩ በአካል ተገኝተው ለትውልድ የሚያስተላልፉበት ነው ብለዋል፡፡
የንግድ ም/ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያምሰፊ ዕውቀት እና የመሪነት ልምድ ባለቤቶች በጡረታ ከተገለሉ በኋላ በቤታቸው የሚውሉ እንጂ ያካበቱትን ሃብት ለትውልድ የሚያስተላልፉበት ባሕል በአገራችን የለም፡፡
ስለዘህ አዲስ ቻምበር በቢዝነስ መሪነት የካበተ ልምድ ያላቸው ዜጎች እየጋበዘ እወቀት ለማሸጋገር የሚያስችል መድረክ ተፈጥሯል ብለዋል ፡፡
በዚህ መድረክ በተለይ ወጣት መሪዎች እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በማስጀመሪያ ሁነቱ ላይ የተጋበዙት ደ/ር አረጋ ይርዳው ቀርበው ከወጣትነት እስከ ጡረታ ዘመናቸው ያካበቱትን ሰፊ የመሪነት ልምድ ሳይሰስቱ አካፍለዋል፡፡
በተለይም ከ6ሺ በላይ ሰራተኞች ያሉትን ግዙፉን የሚድሮክ ኩባንያ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለምራት ሲታጩ በቀጥታ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ስለሚድሮክ በቂ መረጃ በመሰብሰብ ጥናት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ አንድ የሥራ መሪ በስሩ የሚገኙትን ሁሉንም ሠራተኞች በእኩል አይን ማየት አለበት የሚሉት ዶ/ር አረጋ መሪነት ደጋግሞ ማሰብ እና በፍጥነት ውሳኔ መስጠት እንዲሁም አሳታፊ መሆንን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
በመሪነታቸው ወራት በርካታ ከውጪ እና ከውስጥ የሚነሱ ትችቶች እና ፈታኝ ሁኔታዎችን ጆሮ ባለመስጠት ወደ 26 የሚሆኑ እህት ኩባንያዎችን አስተባብረው ለአመታት በጥበብ መምራታቸውን ተናግረዋል፡፡
ይኸው የመማማሪያ እና የልምድ ልውውጥ መድረክ በአዲስ ቻምበር እና በSAK በተባለ አማካሪ ድርጅት ትብብር በወር አንድ ጊዜ የሚዘጋጅ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡