አዲስ ቻምበር ከአባላቱ እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የአብሮነትና የምስጋና ቀንን አከበረ

አዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት/ አዲስ ቻምበር/ እያስመዘገበ ላለው ተቋማዊ ጥንካሬና አሁን ለደረሰበት ደረጃ አባላቱን እና ባለድርሻ አካላትን አመሰገነ፡፡

አዲስ ቻምበር ከአባላቱ እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የአብሮነትና የምስጋና ቀንን ነሃሴ 18፣2015 በስካይላይት ሆቴል በድምቀት አክብሯል፡፡

በእለቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የአዲስ ቻምበር ዋና ጸሃፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም እንደተናገሩት በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የንግድ ምክር ቤቶች ታሪክ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፈው አዲስ ቻምበር ፋና ወጊ ብቻ ሳይሆን በሥራዎቹም አርአያ ለሌሎችም ምክር ቤቶች መቋቋም መሠረት ነው ማለት እንችላለን ብለዋል፡፡

ለዚህም ስኬት አባላቱና የባለድርሻ አካላት ሚናቸው ከፍተኛ ነበርና እናመሰግናለን ሲሉ ተደምጠዋል፡
ንግድ ምክር ቤቱ የንግዱን ማኅበረሰብ ጥቅም ለማስከበርና ተፈላጊ የሆኑ ዘመናዊ አገልግሎቶችን በተሻለ ብቃት ለማቅረብ እንዲያስችለውና ተቋማዊ ቁመናውን በሁለገብ መልኩ እየገነባ ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር አዲስ ቻምበር ከሚያከናውናቸው በርካታ የንግድ ድጋፍ አገልግሎቶች፣ የግንኙነት ተግባራትና የአድቮኬሲ ሥራዎች ዘመኑን ተከትሎ ለማከናወን አሁን ላይ በአደረጃጀት ተሻሽሎና ዘምኖ በሰው ኃይል ተጠናክሮና በፋይናንስ አቅም ጐልብቶ ለአባላቱ የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ላይ የመገኘቱ ሚስጥር በዋናነት የአባላቱ አስተዋጽኦ ነው ብለዋል ፡፡

እያካሄዳቸው ያሉትን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች እያደገ ከመጣው የንግዱ ማኅበረሰብ ፍላጎትና ለውጥ ጋር ለማጣጣም የሚያስችሉ የተለያዩ ተቋማዊ እርምጃዎችንም በመውሰድ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመጪዎቹ ዓመታት እያንዳንዱ አባል ለምክር ቤቱ ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክርና እንደየአቅሙ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት አሻራውን እንዲያኖር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ያለ አባላቱ ተሳትፎ እና አስተዋጽኦ እዚህ ሊደርስ አይችልም ነበር ያሉት ፕሬዚዳንት መሰንበት ብዙዎች የደከሙለት ሥራ ዛሬ ፍሬ አፍርቶ ስናይ ደስታችን እጥፍ ድርብ ነውና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለነበራቸው አብሮነት እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

በአብሮነት እና በምስጋና ቀን ክብረ በአል ላይ ከ150 በላይ አባላት፣የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣የቻምበር ማኔጅመንትና ሰራተኞች፣የዲፕሎማቲክ አባላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ታድመዋል፡፡

አባላቱም የአዲስ ቻምበር አባል በመሆናቸው ያገኟቸውን ጥቅሞች በማንሳት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከነዚህም መካከል የኤችኤስቲ ፓርትነርስ መስራችና ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ግዛው፣ የሞሃን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ሃርሽ ኮታሪ ይገኙበታል። በእለቱም የህንድ እና የኢትዮጵያን የንግድ ግንኙነት የተመለከቱ መረጃዎች ለታዳሚው ቀርበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *