(መጋቢት 30፣2014) በአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት የተመራ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትና ዋና ጸሃፊ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ከክቡር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡።
የንግድና ኢንዱስትሪ ልማትን በማስፋፋትና በማስተዋወቅ እንዲሁም የንግዱ ህብረተሰብ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሚኖረው ሚና ዙሪያ የበለጠ መስራት አስፈላጊ ስለመሆኑ ሁለቱ አካላት ምክክር አካሂደዋል፡፡
የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ንግድ ምክር ቤቱ የግሉን ዘርፍ በማጠናከር በሀገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ ለሚኒስትሩ ገልጸውላቸዋል፡።
በተለይ ለንግድ እና ኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ፤ የንግዱን ሕብረተሰብ በአገሪቱ የኢኮኖሚያዊ ዕድገት ድርሻውን ከፍ ለማድረግ እና ጠንካራ የቢዝነስ ዘርፍ እንዲፈጠር በሚል በተመረጡ 8 የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የአምስት አመት የምክረ ሀሳብ ሰነድ ንግድ ምክር ቤታቸው ለመንግስት ማቅረቡን አስረድተዋል፡፡
የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ተጨማሪ የማሻሻያ ግብአቶችን ንግድ ምክር ቤቱ ስለመስጠቱ አስታውሰው የአዋጁን መጽደቅ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በበርካታ የልማት ስራዎችና በተለያዩ ወቅቶች በዜጎችና በሀገር ላይ ችግር ሲገጥምም ቀድሞ በመድረስ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ለሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ በቀጣይነትም በጦርነቱ ወቅት የወደሙትን አካባቢዎች መልሶ በማቋቋም ረገድ ከግሉ ዘርፍ እና ከመንግስት ጋር በመሆን የአይነትና የቁሳቁስ ድጋፍን ጨምሮ የግሉ ዘርፍ እንዲነቃቃ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ብለዋል። በዚህ ረገድ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር አብሮ መስራት በሚቻልበት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር አቶ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር ግንኙነት በመፍጠርና በመቀራረብ በትልልቅ እና አንኳር ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቀጣይነት ያለው እንቅስቃሴ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡። በተለይ አዲስ ቻምበር የግሉን ዘርፍ አበይት ጉዳዮች በማንሳት ሀገራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማመቻቸት ፣ የፖሊሲ ግብአት በመስጠት፣ የንግድ ድጋፍ አገልግሎት በማቅረብ ተወዳዳሪነትን ማስፈን እና የግሉ ዘርፍ በስነምግባር እንዲመራና ማህበራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ለማስተማር እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል ።
የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/1995 ከወቅቱና ከዘመኑ ጋር አብሮ እንዲሻሻል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ይህንን ጉዳይ በእጅጉ በማጤን የአዋጁን የማሻሻያ ረቂቅ በማጠናቀቅ በሚመለከተው እንዲጸድቅ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡።
ንግድ ምክር ቤቱ በበርካታ የልማት ስራዎችና በችግር ወቅት ቀድሞ በመድረስ ለተጫወተው ሚና ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል፡። በቀጣይም ንግድ ምክር ቤቱ ከአባላቱና ከመንግስት ጋር በመሆን ስራ አጥነትን እና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል ።
በአፍሪካ ነጻ የንግድ ገበያ ዙሪያ የግሉ ዘርፍ ሁልጊዜም ብቁ፣ዝግጁና ተወዳዳሪ እንዲሆን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በአጋርነት ልንሰራበት ይገባል ብለዋል፡፡
የአዲስ ቻምበር ዋና ጸሃፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በበኩላቸው ንግድ ምክር ቤቱና ንግድ ሚኒስቴር በተለያዩ የንግድና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ አብረው መስራታቸውን ተናግረዋል፡። በተለይም ሀገሪቱ የንግድ ፖሊሲ እንዲኖራት አዲስ ቻምበር በርካታ የአድቮኬሲ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው መንግስትም ይህንን ጉዳይ በእጅጉ በማጤን የንግድ ፖሊሲ ረቂቅ እንዲዘጋጅ ማድረጉ ለምክር ቤታችን ትልቅ ውጤት ነው ብለዋል ።
የስራ እድል ፈጠራን በተመለከተ አዲስ ቻምበር በርካታ ወጣቶችን እና ሴቶች የሚያቅፉ የቢዝነስ ማበልጸጊያ ማእከልን ማቋቋም የመሰሉ ፕሮጀክቶችን እየተገበረ መሆኑን ዋና ጸሃፊው አስረድተዋል፡፡
ከግሉ ዘርፍ ጋር ወጣቶች እንዲገናኙ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሺበሺ በዚህ ጉዳይ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት አለን ሲሉ ለሚኒስትሩ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡