የእርሻ ውጤቶች እና የማቀነባበሪያ ዘርፉ በብዙ ችግሮች የተተበተበ እና ከሌሎች አገራት ጋር ሲወዳደር ገና ብዙ እንደሚቀረው የአዲስ ቻምበር ጥናት አመለከተ፡፡
የፍራፍሬ ልማት በሀገሪቱ የ10 ዓመት የኢንዱስትሪ የልማት መርሐግበር ውስጥ የቅድሚያ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፍ አንዱ ነው ተብሏል፡፡
ነገርግን በመሬት ላይ ያለው እውነታ የተባለውን ያህል አይደለም ያለው ጥናቱ፤ አገራችንም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጪ ምንዛሬ እንዳላገኘች ተጠቁሟል ፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤትም ይህን የተመለከተ አንድ ጥናት በማስጠናት ከባለድርሻዎች ጋር የፖሊሲ ውይይት አካሂዷል፡፡
በዘርፉ ባለሙያ በሆኑት አቶ ታምራት ታደለ የቀረበው የጥናት ወረቀት አገራችን 6 የሚሆኑ ዋና ዋና የፍራፍሬ ኮሪደሮች አላት ብለዋል፡። የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ፤የአባያ ፤ የጣና ተፋሰሶች፤ የቤንሻነጉል-ጉሙዝ፤ የጅማ፤የራያ እና የሐረርጌ ሸለቆዎች ሲሆኑ በአመት የሚሰበሰበው ምርት ደግሞ ወደ 1 ሚሊየን ቶን አቮካዶ፤ብርትኳን፤ሙዝ ፤ ፓፓያ እና ስትሮቤሪ የመሳሰሉት ፍራፍሬዎች ናቸው ፡፡
በተለይ አቮካዶ በአመት እስከ 1 ሚሊየን ኩንታል ድረስ ይመረታል ብለዋል፡፡
እንደ ጥናቱ ከሆነ 90 በመቶ የሚሆነው የአገራችን የፍራፍሬ ምርት የምትገዛው ጎረቤት አገር ጂቡቲ ናት፡፡ እስከ ባለፈው 2 አመት ድረስም ከዘርፉ የሚገኘው የውጪ ምንዛሬ 2 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ያህል ብቻ ነው ተብሏል፡፡
የፍራፍሬ ምርታማነታችን አንደ ቻይና እና ሕንድ ከመሳሰሉ የዘርፉ አምራች እና ላኪ አገራት ጋር ሲነጻጸር አዚህ ግባ ዪባል አይደለም ይላሉ አቶ ታምራት፡፡
የአገራቸንን የፍራፍሬ ምርታማነት ቀይደው ከያዙት መዋቅራዊ እና የፖሊሲ ችግሮች መካከል ፍራፍሬ አምራቾች በትናንሽ የገበሬ እርሻዎች ላይ የተመሠረተ መሆኑ፤ የፍራፍሬ ምርቶች በቶሎ የሚበላሹ በመሆናቸው በቂ መሰረተ ልማት አለመበኖር ፣በዘርፉ ያሉ የመንግሥት ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶች በአንድ ልብ ተቀናጅተው ለውጪ ገበያ እስኪላክ አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠት አለመቻላቸው የዘርፉ ትልቅ ፈተና ነው ተብሏል፡፡
የአትክልት ዋጋም የሚወሰነው በተቋማዊ እና በሕጋዊ አሠራር አለመሆኑ ዛሬ ላይ የፍራፍሬ ዋጋ ሰማይ ደርሶ ፍራፍሬ መመገብ ከቅንጦት እየተቆጠረ መሆኑ ተገልጿል ፡፡
የኢትዮጵያ የአበባ ፣አትክልት እና ፍራፍሬ አምራች እና ላኪዎች ማሕበር ኤግዘኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ቴድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው ለማሕበራቸው አባላት ሰልጠና ለመስጠት ባለሙያዎችን ከውጪ ድረስ በማስመጣት የአቅም ግንባታ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡
እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለፃ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው በፍራፍሬው እርሻዎች አካባቢ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርመር ተቋማት የእውቀት ድጋፍ እንዲያደርጉ መንግሥት ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
መንግሥት ለፍራፍሬ አምራቾች እና አቀናባሪዎች ከቀረጥ ነጻ የግብር እፎይታዎችን ተግባራዊ ማድረጉን የገለጹት ከንግድ እና ቀጠናዊ ትሰስር ሚኒስቴር የመጡት አቶ ሐጎስ አባይ ፤ እንደ ስኳር ያሉ ግብዓቶችን አቅም በፈቀደ መጠን ለአቀናባሪዎች ለማዳረስ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት ያስቀመጠው ማበረታቻ አንደ ተጠበቀ ሆኖ የውጪ ምንዛሬ እጥረት አሁንም ያልተፈታ ማነቆ ነው ያሉት ጥናት አቅራቢው መንግሥት ከባድረሻዎች ጋር በመመካከር ሕጋዊ አሠራር ዘርግቶ በመሃል ያሉ ደላሎች ከፍራፍሬ ዕሴት ሰንሰለት ሥርዓት ውስጥ ማስወጣት አለበት ብለዋል፡፡
አንዲሁም ተቆጣጣሪ የመንግሥት መ/ቤቶች የፍራፍሬ መሰብሰበያ ወቅቶችን ማዕክል አድርገው የአንድ መሥኮት አገለግሎት መስጠት አለባቸው ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የአዲስ ቻምበር ም/ዋና ጸሀፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ነጋዴው ሕብረተሰብ በተሰማራባቸው የተለያዩ የንግድ ዘርፎች የሚስተዋሉትን የአሰራር እና የፖሊሲ ችግሮችን በማጥናት ንግድ ምከር ቤቱ ነቅሶ እያወጣ የመፍትሔ ምክረ-ሃሳቦችን ለመንግሥት ሲያቀርብ ቆይቷል ብለዋል፡፡
ከዚህ ጥናት የተገኙ የፖሊሲ ሕጸጾችን ከነመፍትሔ ምክረ-ሃሳቦች ለሚመለከተው የመንግሥት አካል በማቅረብ ማሻሻያዎች እንዲደረግባቸው ጥረት ይደርጋል ብለዋል፡፡