ስምምነቱ የምክር ቤቱን አገልግሎት አሰጣጥ ያዘምነዋል ተብሏል፡፡
አዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና ህብረት ባንክ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን በአዲስ ቻምበር በኩል የፈረሙት የምክር ቤቱ ፕሮዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ሲሆኑ ከህብረት ባንክ በኩል ደግሞ የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ ናቸው፡፡
የአዲስ ቻምበር ፕሮዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ እንዳሉት ፡- ምክር ቤቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በፋይናንስ ዘርፍ ከህብረት ባንክ ጋር በጋራ ይሰራል፡፡
ምክር ቤቱ የአሰራር ለውጥ ማድረጉን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቷ ስምምነቱ የምክር ቤቱን አገልግሎት አሰጣጥ ያዘምነዋል ብለዋል ፡፡
የህብረት ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ በበኩላቸው ስምምነቱ ግንኙነቱን ለማጠናከር ትልቅ መሰረት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ መላኩ ገለፃ ፡- ህብረት ባንክ የምክር ቤቱን የአባላት ክፍያ አሰባሰብን በዘመናዊ የፋይናስ ስርአት ማእቀፍ ውስጥ ከማስገባት በተጨማሪ በፋይናንስ ዘርፍ በኩል በሚከናወኑ የቻምበር ሁነቶች ላይ በመሳተፍ ግንኙነቱን ለማጠናከር ፍላጎት አለው፡፡
በተጨማሪም የምክር ቤቱ ዋና መሰሪያ ቤት ህንፃ ግንባታን ጨምሮ በሁሉም ፕሮጀክቶች ላይ ባንካቸው በተቻለ መጠን ተሳታፊ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።
የምክር ቤቱ ሰራተኞች የብድር / የፋይናንስ / አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል ባንኩ ከምክር ቤቱ ጋር ሊሰራባቸው ከተሰማማባቸው መስኮች ዋነኞቹ ናቸው ፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በበኩላቸው የመግባቢያ ስምምነቱ በፋይናንስ ዘርፍ በተለይም በስልጠና፣ በጋራ ለሚሰሩ ማህበራዊ ሃላፊነቶች ፣ ከአባላት በሚሰበሰብ ክፍያ እና በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ዙርያ በጋራ ለመስራት ያስችላል ብለዋል፡፡
የአሁኑ ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ፀሐፊው በቀጣይ ከሌሎች ባንኮችም ጋርም በፋይናንስ ዘርፍና በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡