የአዲስ አበባ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የ20ኛ አመት ምስረታ በዓሉን ማክበር ጀምሯል፡፡
ምክር ቤቱ የ20ኛ ዓመት የምስረታ በአሉን ማክበር በጀመረበት ወቅት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ አቶ ሃሰን መሃመድ እና ሌሎች ባለድርሻዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የአምራች ዘርፉ ስኬቶች፡ተግዳሮቶች እና የወደፊት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል ፡፡
በውይይቱ አምራች ዘርፉ በመንግስት ትኩረት የተሰጠው ቢሆንም ብቁ የሆነ የሰው ሃይል ባለመኖሩ ምክንያት ውጤታማ መሆን እንዳልቻለ ተጠቁሟል ፡፡
የቴክኒክ እና ሞያ ተቋማት ለኢንዱስትሪዎች ብቁ ባለሞያ ከማቅረብ አንጻር በሚገጥሙ ችግሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ለውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶ/ር ገነነ አበበ አምራች ዘርፉን ከሚገዳደሩት ችግሮች መካከል ቀዳሚውን ቦታ የሚይዘው የበቁ ባለሞያዎች አለማግኘት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የቴክኒክ እና ሞያ ተቋማት ላይ ባለው የአመለካከት ችግር ምክንያት አምራቾች ከነዚህ ተቋማት የሚወጡ ባለሞያዎች ላይ እምነት ጥሎ ቀጥሮ ለማሰራት ችግር እየተፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ተቋማቱ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እና የማሽነሪ ግብአት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ተከትሎ ከሌሎች የትምህርት ተቋማት ባነሰ በጀት የሚያዝላቸው መሆኑ በራሱ ተማሪዎች ብቁ ባለሞያ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
አምራች ዘርፉ የሚፈልገውን ባለሞያ ለማግኘት ከቴክኒክ እና ሞያ ተቋማት ጋር ያለውን የቅንጅት ስራ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ እና በገንዘብም ሆነ በሞያ ስልጠና መደገፍ ወሳኝ መሆኑን በምክረ ሃሳባቸው አቅርበዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የአምራች ዘርፉ ስኬቶችን እና ተግዳሮቶችን እንዲሁም የፋይናንስ ተደራሽነትን እና ዲጂታል ፋይናንስን የተመለከቱ ለውይይት መነሻ የሆኑ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡