(ሰኔ 7፤ 2016 ፤ አዲስ ቻምበር)
የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከተቋቋመባቸው አላማዎች አንዱ የፖሊሲ አድቮኬሲ ስራዎችን በማካሄድ ለንግድና ኢንቨስትመንት አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ማድረግ ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ምክር ቤቱ ባለፉት ጊዜያት በርካታ የምክክር መድረኮችን በማመቻቸት ቁልፍ ባለ ድርሻ አካላት እንዲመክሩና የተሻሉ የንግድ ህጎችና ፖሊሲዎች እንዲወጡና እንዲተገበሩ ከፍተኛ ሚናን ተጫውቷል፡፡
የዚህ አንድ አካል የሆነው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ በታክስ ዙርያ ትኩረቱን በማድረግ ተካሂዷል፡፡
“የታክስ ስርአት አተገባበር በግሉ ዘርፍ ላይ ያለው ተጽእኖ” በሚል ርእሰ ጉዳይ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የምክክር መድረክ ቁልፍ ባለ ድርሻ አካላትን በማገናኘት በግብር አወጣጥና አተገባበር ዙርያ ሰፊ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት መድረክ ነበር፡፡
በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ ዋና ጸሀፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም የግብር ጉዳይ ከበርካታ አመታት ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ ችግር መሆኑን ተናግረው እንዲህ አይነት ችግሮችን ለመፍታት ምክር ቤታቸው ወሳኝ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ፤ የፖሊሲ ግብአቶች የሚሰበሰቡበትና አመቺ ፖሊሲዎች እንዲወጡና ተግባራዊ እንዲደረጉ ምክር ቤቱ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ ፕረዚደንት መሰንበት ሸንቁጤ የንግዱ ማህበረሰብ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ በማስታወስ ነገር ግን ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባትና የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ለማስፈን ጤናማ፣ፍትሐዊና ቀልጣፋ የሆነ የግብር ስርአት መኖር ወሣኝነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ ፕረዚደንት አክለው እንዳሉት የሚወጡ አዋጆችና ደንቦች ከመውጣታቸውም በፊት ሆነ ከወጡ በኋላ የሚመለከታቸውን አካላት በሚፈለገው ልክ የማያሳትፉና በግንዛቤ ማስጨበጥ ዙሪያ ክፍተት ሲታይባቸው ይስተዋላል ያሉ ሲሆን ይህንን ችግር ለመቅረፍ ንግድ ምክር ቤቱ ከህግ አውጪውም ይሁን ከአስፈጻሚው አካል ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን በመድረኩ ላይ ገልጸዋል፡፡
“የታክስ ስርአት አተገባበር በግሉ ዘርፍ ላይ ያለው ተጽእኖ ፤አንድምታ” በሚል የተዘጋጀው የምክክር መድረክ ለውይይት የሚውሉ ጹሁፎች በምሁራንና በሚመለከታቸው ባለሙያዎች የቀረቡ ሲሆን ሰፊ ያሉ ሀሳቦችና ግብአቶች ቀርበውበታል፡፡
ከተነሱ ሀሳቦችና ምልከታዎች መካከል የኢትዮጵያ የታክስ ምጣኔ ከጥቅል አመታዊ ምርት ጋር ሲነጻጸር እየቀነሱ መምጣቱ፤ የታክስ ሪፎርሞች ከተቋማት ግንባታ ፤ከሰለጠነ የሰው ሀይል አንጻር ክፍተቶች እንዳሉበት፤ የታክስ ሪፎርሞች ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ አለመሆናቸው፤ የታክስ ፖሊሲ ለውጦችን በየጊዜው ከሚለዋወጠው ኢኮኖሚ ጋር በማነጻጸር ለውጥ ያለማድረግ ክፍተቶች በዋናነት ተጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የምክክር መድረኩ በንብረት ግብርና በኢክሳይስ ታክስ ዙርያ ሰፋ ያሉ ውይይቶች የቀረቡ ሲሆን ከተነሱት ሀሳቦች መካከል በኢትዮጵያ የንብረት ታክስ ለረጅም አመታት ችላ መባሉ አሳሳቢ መሆኑ፤ የንብረት አመዘጋገብ ስርአት ደካማ መሆን፤ የቅንጅታዊ አሰራር መጓደል፤ የታክስ ከፋዮች ቻርተር አለመኖር፤ የታክስ ከፋዮችን መብት ሊያስከብር የሚችል ተቋም መኖር፤ የታክስ ግጭት አፈታት ረጅምና አሰልቺ መሆን በዋናነት ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡
ኤክሳይስ ታክስን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ያሉ የኢክሳይስ ታክስ ህጎች ጉዳትና ጠቀሜታቸው ላይ የኩባንያ ልምድ የቀረበ ሲሆን በባለፉት አራት አመታት ኤክሳይስ ታክስ ለሁለት ጊዜ ክለሳ እንደተደረገበት እንደ መልካም ተነስቷል፡፡
ነገር ግን የኤክሳይስ ታክስ ህጎች ሲከለሱ የሀገር ውስጥ ኩባያዎች ላይ ከመጠን በላይ ታክስ በመጣል ህልውናን በማይፈታተን መልኩ መሆን እንዳለበት እና ለህገ ወጥ ንግድ በር ከፋች መሆን እንደሌለባቸው ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ “የታክስ ስርአት አተገባበር በግሉ ዘርፍ ላይ ያለው ተጽእኖ ፤አንድምታ” የምክክር መድረክ ለፖሊሲ ግብአት የሚረዱ በርካታ ምክር ሀሳቦች የተዳሰሱበት ሲሆን በርእሰ ጉዳዩ ዙርያ ከተነሱ ምክር ሀሳቦችና ምልከታዎች መካከል የኢትዮጵያ የታክስ አሠራር እና አተገባበር ቀልጣፋና ለንግድ አሰራር አስቻይ እንዲሆን አሁን ያለው የታክስ ፖሊሲና ሕግ መመሪያ ወደፊት ከሚታሰበው የግል ዘርፉ ሚና አኳያ መቃኘት እንዳለበት፤ የታክስ ሪፎርም በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችሉ ተቋማት፤ ስትራቴጂ፤ዝርዝር ህጎች፤ እንደ ግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ላሉ ዘርፎች ትኩረት መስጠት፤ በታክስ አሰባሰብ ሂደት ውስጥ ቴክኖሎጂን መጠቀም፤ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል አሰራር የመፍጠር አስፈላጊነት፤ የታክስ የመሰብሰብ አቅምን ይበልጥ ማሳደግ፤ ፍትኃዊና ተጠያቂነት ያለበት የታክስ ስርአትን መፍጠር፤ ግልጽ የሆነ የህግ ማእቀፍ ማዘጋጀት፤ የታክስ ግንዛቤ እንዲያድግ ማድረግ፤ የታክስ ከፋዮች ቻርተር ማዘጋጀት የሚሉት ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በመጨረሻም ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት የተሰበሰቡ ግብአቶችን በማጠናቀር ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለፖሊሲ ግብአትነት እንደሚውሉ ከምክር ቤቱ ተገልጿል፡፡