በሶስት ዙሮች ተከፍሎ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው የአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽንና ኤግዝቢሽን ማዕከል የመጀመሪያ ዙር ግንባታው 70 በመቶ መድረሱ ተነገረ።

የማዕከሉ አንድ አካል የሆነው የንግድ ማዕከል ግንባታ ደግሞ  ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ ተነገሯል።

ዛሬ ማዕከሉ በሚገነባበት ስፍራ በተካሄደው የአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽንና ኤግዝቢሽን ማዕከል አክሲዮን ማህበር 11ኛ መደበኛ እና 11ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው ግንባታው የደረሰበት ደረጃ የተነገረው።

በ2010ዓ.ም የተጀመረው የማዕከሉ ግንባታ የመጀመሪያ ዙር በ2012 ዓ.ም መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም በግንባታ  ዕቃዎች ዋጋ መናር እና በኮቪድ 19 ምክንያት ከውጭ ሃገር ዕቃ ለማስገባት አስቸጋሪ ሁኔታ በመፈጠሩ  ሂደቱ በተፈለገው ፍጥነት አለመሄዱ ተጠቅሷል።

ግንባታውን ለሚያከናውነው ተቋም ለሶስተኛ ጊዜ ውል በማራዘም  ከሚያዚያ 2014ዓ.ም  ጀምሮ 540 ቀናት ተጨምረውለታል።

ስለሆነም ግንባታው በህዳር 2016 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል የስራውን ሂደት ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባዔው ያቀረቡት የዳሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መሀመድ ኑርሳኒ።

በስተመጨረሻም የ2014ዓ.ም የስራ ክንውን ሪፖርት እና ኦዲት ሪፖርት ቀርቦ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *