የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ከአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ለዳያስፖራው ማህበረሰብ በከተማዋ ብሎም በሀገሪቱ ስላለው የኢንቨስትመንት ሁኔታ ተጨባጭ መረጃ እንዲኖራቸው የሚያስችል መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኢንቨስትመንት አዋጅ ፤ ደንብና መመሪያ መሰረት በአምራች፤ በአገልግሎት እና በግብርና ዘርፍ በተፈቀዱ ማበረታቻዎች ዙሪያ የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቧል፡፡
የኮሚሽኑ የፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጫካ በሰነዱ ላይ በየዘርፉ የሚሰጡ የቀረጥ እና ታክስ ነጻ፤ የገቢ ግብር እፎይታ ማበረታቻዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ዳያስፖራ ባለሀብቶች ቢሰማሩባቸው አዋጭ የሆኑ የኢንቨስትመንት አማራጮች በዝርዝር ተገልጸዋል፡፡
ቅድሚያ የሚሰጣቸው እንዲሁም አዋጭ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተብለው የተለዩት በገበያ ተፈላጊነት ፤ በውጭ ምንዛሬ ግኝት እና በስራ እድል ፈጠራ አንጻር ታይተው የቀረቡ መሆናቸውን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ለዳያስፖራው እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
ለአብነትም የኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥን በተመለከተ ዳያስፖራው በተለያየ ቦታ ያገኝ የነበረውን አገልግሎት በአንድ ስፍራ እንዲያገኝ በኮሚሽን መ/ቤቱ ውስጥ ማእከል መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡
ዳያስፖራው ማህበረሰብ የኢንቨስትመንት ፍላጎት ባሳየባቸው መስኮች ላይ ለመሰማራት የኢንቨስትመንት ፈቃድ እና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ሀገር ቤት መምጣት ሳይጠበቅበት በበይነመረብ (ኦንላይን) መገልገል የሚችልበት አሰራር በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል፡፡(Ethio investment Forum)