የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ለኢኮኖሚው እና ለግሉ ዘርፍ ትኩረት ይደረግ-ርእሰ አንቀጽ

የኮሮና ቫይረስ የአለምን አጠቃላይ የኑሮ ቅርጽና ኢኮኖሚያዊ መዋቅርን በመረበሽ ዓለም ከረጅም ዘመን በኋላ የገጠማት ክስተት መሆኑንም ለማናችንም ግልጽ ነው። በዚህም ምክንያት ሀገራት ድንበራቸውን ዘግተዋል፣ዜጎች ወደ ፈለጉበት ቦታ የመንቀሳቀስ ሂደታቸውም ከመግታት ባለፈ ሰዎች የሚሰባሰቡባቸው ሁነቶች ቁጥርም ከቫይረሱ መከሰት በኋላ ወደ ምንምነት ተጠግቷል ፡፡

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ትብብርን ይጠይቃል፡፡ በበሸታው ሳቢያ ክፉኛ ኢኮኖሚው እነዳይጎዳና ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ ኢንዱስትሪዎችንና አገልግሎት ሰጪዎችን በዚህ አጋጣሚ ሊደግፉ የሚቻልባቸውን መንገዶች መመቻቸት አለባቸው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ኢኮኖሚው ላይ ትኩረት ማድረግ የግድ ነውና፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል ጥሩ ተሞክሮ ያላቸውን የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የስራ ኩባንያዎች ልምድና ተሞክሮ ማህበረሰቡ ሊያውቅም ይገባል፡፡

ቫይረሱ ከደቀነው የነዋሪዎች የመንቀሳቀስና በጋራ የመኖር ባህል ፈተና በከፋ መልኩ፣ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን እና የብዙሀን የአለም ዜጎች ሰርቶ መግባት ፈተና ውስጥ ገብቷል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችም ስራቸውን አጥተው የመኖር ፈተና ውስጥ ወድቀዋል ፡፡

በኢትዮጵያም የቫይረሱ መግባት ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ ኢኮኖሚያዊም ይሁን ማህበራዊ ፈተናዎችን ደቅኗል በዚህም የዜጎች እንቅስቃሴ ተገድቧል፣ የንግድም ይሁን የማምረቻ ኢንዱስትሪው ችግር ውስጥ ወድቋል፣ በኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ሳቢያ ስራቸውን ካጡ ዜጎች ባለፈ በተለይም በእለት በሚገኝ ገቢ ላይ ኑሮአቸውን የመሰረቱ ዜጎች ከምንጊዜውም በላይ አደጋ ላይ ወድቀዋል። የአገልግሎትና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች መቀዛቀዛቸው በውስጣቸው ያለው የሰው ሃይል ከስራ ውጪ ሆኗል፡፡

ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን መታደግ እና የድጋፍ ስራዎች ችግሮችን ለአጭር ጊዜ ለማለፍ ቢያግዙም፤ ዘላቂ መፍትሄ መሆን ግን አይቻላቸውም ፡፡ ዘላቂውና አዋጪው መፍትሄ የአኮኖሚውን ቅርጽ መጪውን ጊዜ ባገናዘበ መልኩ መዘርጋትና የስራ እድል በሚፈጥሩት የግል ዘረፎችን መደገፍ ለነገ የሚባል መሆን የለበትም።
የግል ዘርፉ ለብዙ ሰዎች የስራ እድልን መፍጠር መቻሉ ዘርፉ ላይ ትኩረት መድረግ አለበት፡፡

በወረርሽኑ የሚጎዱ ስራ ዘርፎች በተለይ የጉዞ፤ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ፣የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ፣ ችርቻሮና አከፋፋዮች፣ትራንስፖርት ዘርፍ፣አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ፣የአገልግሎት ዘርፎች መደገፍ ይኖርባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች፣ ሕጎች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች እንዲሁም በልዩ ልዩ ንግድ ነክ ጉዳዮች ላይ የንግዱ ህብረተሰብና መንግስት ተቀራርበው የሚወያዩባቸውን የግንኙነት መድረኮች በመፍጠር ችግሮች ስር ሳይሰዱ ቶሎ ቢቀረፉ መልካም ነው፡፡

በዚህ ወቅት ወረርሺኙን ከመከላከል ጎን ለጎን ስነምግባርን የተላበሰና ተወዳዳሪ የሆነ የግል ዘርፍ ለመፍጠር የግንዛቤ ስራ ለመስራት ከንግድ ምክር ቤቶች በተጨማሪ ንግድ ሚኒስቴርን የመሳሰሉ አደረጃጀቶች ቁልፉን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል፡፡