የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከዳሸን ባንክ እና ከጊፍት ሪልስቴት በተገኘ እገዛ በቦሌ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ የተቸገሩ ወገኖች መጭውን የትንሳኤ እና ኢድ አልፈጥር በዓልን አስመልክቶ የዘይት እና የዱቄት ድጋፍ አድርጓል፡፡
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ በስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት መሰል የኢኮኖሚ ችግር በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ አለመሆኑን እና ችግሮቹን ለማለፍ ሁሉም በየአቅሙ መስራት እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል፡ምክር ቤቱም የሚያደርገውን ድጋፍ ዘላቂ የኢኮኖሚ ለውጥ ማምጣት የሚያስችልበትን መንገድ በመፍጠር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አለም ጸሃይ ሽፈራው በበኩላቸው ምክር ቤቱ መሰል ድጋፎችን ሲያደርግ ለሶስተኛ ግዜ መሆኑን አንስተው፡በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው በመሄድ ክፍለ ከተማውን በማገዝ ረገድ ምክር ቤቱ ከጎናቸውእንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም መንግስት ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ቢሆንም ፈተናዎች መግጠማቸው የበለጠ ጠንክሮ የሚያሰራ እና በመተባበር ሊታለፉ የሚችሉ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት ከሚያደርጋቸው ጥረቶች ውስጥ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ከዚህ ቀደም ሲያደርገው እንደነበረው መቶ ለሚደርሱ ችግረኞች ድጋፉን አድርጓል፡፡