ችግረኞችን በዘላቂነት ራሳቸውን አንዲችሉ እየሠራ ነው
የአዲስ ቻምበር ፕሬዝደንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ከቦሌ እና ከለሚ ኩራ ክ/ከተሞች ለተውጣጡ 185 ለሚሆኑ ወገኖች እርዳታውን ባስረከቡበት ስነስርዓት ላይ ዛሬ ተረጂ የሆኑት ወገኖቻችን በሁኔታዎች መካከል በተፈጠሩ አጋጣሚዎች እንጂ የየራሳቸው ሙያ እና መተዳደሪያ ያላቸው፤ለሌሎች የሚተርፉ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በዚህ ችግር ወቅት የንግዱ ሕብረተሰብ የሚያደርገው ድጋፍ ቢያንስ ከአለን ላይ በችግር ላይ ለሚገኙ ወገኖች ማካፈል አለብን ከሚል የሞራል ግዴታ በመነሳት ነው ብለዋል፡፡
የተደረገላቸው የዘይት እና ደረቅ ምግቦች ልገሳ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ እንዳልሆነ ወ/ሮ መሰንበት አስታውሰው ተረጂዎችን እንደየሙያቸው በሥራ ተሰማርተው በዘላቂነት ራሳቸውን ረድተው ፤ ለአገራቸው የሚተርፉ ዜጎች እንዲሆኑ ንግድ ም/ቤቱ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
አዲስ ቻምበር “የግሉ ዘረፍ ጥምረት በኑሮ ውድነት ላይ” በሚል የጀመረው ፕሮጀክት አባላቱን በኮርፖሬት ማሕበራዊ ሃላፊነት ሥራዎች ላይ በሰፊው በማንቀሳቀስ የኑሮ ውድነቱ ክፉኛ ለጎዳቸው የከተማይቱ ነዋሪዎች ድጋፍ ለማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ሠናይ ዓላማ ምላሽ በመስጠት የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉ የግል ኩባንያዎች በተረጂ ወገኖች ስም ፕሬዝደንቷ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የቦሌ ክፍለከተማ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራው በበኩላቸው የተጀመረው የእርስበርስ የመደጋገፍ ባሕል የዛሬ ተረጂዎች ነገ ራሳቸውን የቻሉ እና በተራቸው ሌሎችን የሚረዱ ዜጎች እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
ትልቁ ቁም ነገር ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች የዛሬው ችግር የሚያልፍ መሆኑን ተገንዝበው ለወደፊቱ በመንፈሰጠንካራነት ራስን ለመቻል መነሳሳት አለባቸው፡፡
መንግሥት ደጋፊ የሌላቸውን እና አቅመ ደካሞችን በዘላቂነት ለመርዳት ሰው-ተኮር የሆኑ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡
ንግድ ም/ቤቱ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናችውን አቀርበዋል፡፡
ደርባ ስሚንቶ ፋብሪካ፤የቀስተደመና ስፖንጅ ፋብሪካ ፤የጊፍት ሪል ስቴት እና ፊሊጶስ እና ቤተሰቡ ኃ.የተ.ግ.ማሕበር በጋራ ድጋፍ ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአዲስ ቻምበር ሀሳብ አፍላቂነት የተጀመረው “የግሉ ዘረፍ የጥምረት በኑሮ ውድነት ላይ” የተሰኘው ፕሮጀክት ከክቡር የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የሚተገበር ሲሆን ቀደም ሲል በቂርቆስ ከ/ከተማ በ2ወረዳዎች ለሚገኙ ወገኖች ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡