የአዲስ ቻምበር ፕረዚደንት መሰንበት ሸንቁጤ የ2016 አ.ም የምክር ቤቱ ስኬትና ተግዳሮት እንዲሁም የ2017 አ.ም የምክር ቤቱን የወደፊት የትኩረት አቅጣጫን በተመለከተ ከአዲስ ቻምበር ሚዲያ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

ምክር ቤቱ የንግዱን ህብረተሰብ ለማገልገል በአዋጅ እና በቦርድ የሚመራ ተቋም መሆኑን ፕረዚደንቷ ገልጸዋል፡፡
የንግድ እንቅስቃሴን አስመልክቶ የንግዱ ማህበረሰብ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በሚከሰቱ ችግሮች ምክንያት በርካታ እንቅፋቶች እንደገጠሙት ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ግን ምክር ቤቱ በነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በማለፍ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል በተለይም ምክር ቤቱ በርካታ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የንግዱን ማህበረሰብ ማወያየት መቻሉን የተናገሩ ሲሆን በተግዳሮቶች የታጠረው ምክር ቤት በ2016 አ.ም በርካታ ስራዎችን መስራቱን ገልጸዋል ከነዚህም መካከል ለመንግስት የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን የሰጠበት እና በቻምበር ደረጃ ደግሞ የንግዱን ማህበረሰብ ይበልጥ ለማገልገል ጥረት ማድረግ መቻሉን ገለጸዋል፡፡
የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማሳለጥ የሰላም መኖር አስፈላጊ እንደሆነ የተናገሩት ፕረዚደንቷ ምርትን ለማምረት ሆነ የተመረተውን ለመሸጥ ሰላም ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ስለሆነም ምክር ቤቱ ከሚመለከታቸው የመንግስት እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን የምክር ቤቱን አባላት ያሳተፉ ንግድ ምክር ቤቶች ለሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና የሚቃኙ የምክክር መድረኮች መካሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ በ2017 አ.ም በርካታ እቅዶች እንዳሉት የተናገሩት ፕረዚደንት መሰንበት ይበልጥ የነጋዴው ድምጽ ሆኖ እንዲያገለግል ፤ ዘመናዊ አሰራሮችን ተከትሎ መሄድ እንዳለበት እና የውጭ ሀገራት የንግድ ምክር ቤቶችን ተሞክሮ መቅሰም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን የታሰቡ እቅዶችን ለማሳካት አሁንም ቢሆን አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የንግዱ ማህበረሰብም ሆነ ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የግል ዘርፉ የሰላም ግንባታ ላይ መስራት አለበት ያሉት ፕረዚደንቷ ባለ ሀብቶች በተለይም ሙዋለ ንዋያቸውን በማፍሰስ የስራ እድል እንዲፈጠር በማድረግ በተዘዋዋሪ ለሰላም ግንባታ አስተዋጾ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የተረጋጋ ማህበራዊ ህይወት እንዲፈጠር በኢኮኖሚ የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማገዝ ከዚህ በፊት የነበሩ ተሞክሮዎችን በአዲሱ አመት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የምክር ቤቱ ኀላፊነት መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
መንግስት ንግድ ምክር ቤቶችን በመደገፍ ጠንካራ የግል ዘርፍ እንዲፈጠር የሚረዱ ተቋማት እንደሆኑ የሚናገሩት ፕረዚደንቷ የግል ዘርፉ ማደግ ከቻለ የተረጋጋ ሀገር መፍጠር እንደሚቻል፤የሚወጡ ህጎችና ፖሊሲዎች የግሉን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ፤ከግሉ ዘርፍ ጋር ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ማጠናከር እና መንግስት በ10 አመቱ የልማት እቅድ ውስጥ ለግሉ ዘርፍ እድገት የሰጠውን ቦታ በአግባቡ መተርጎሙን ማሳየት አለበት ብለዋል፡፡
የግል ዘርፉን ለማሳደግ በሚደረገው ሂደት ውስጥ መንግስት ከንግድ ምክር ቤቶች ጋር አንድ ላይ በመስራት ሊያሳካው እንደሚገባ የተናገሩ ሲሆን ንግድ ምክር ቤቶች በአለምአቀፍ ደረጃ ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸውና በተለያዩ ጊዜያት የነበሩት መንግስታት የተለያየ አይነት ቀረቤታና ድጋፍ ማድረጋቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በመጪዎቹ አመታት ምክር ቤቱ ለንግዱ ህብረተሰብ የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ በማስፋት ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ፕረዚደንቷ የገለጹ ሲሆን የጽህፈት ቤቱን ባለሙያዎች አቅም ማጠናከርና አለምአቀፍ ልምድ እንዲኖራቸው ማድረግ ፤ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ በመስራት ተወዳዳሪ ምክር ቤትና የግል ዘርፍ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ለግሉ ዘርፍ ማደግ ሰፋፊ እድሎች እንዳሉ የተናገሩት ፕረዚደንቷ እንደ ካፒታል ማርኬት፤ የውጭ ባንኮች መምጣት አለምአቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ መጀመራቸው ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ንግድ ምክር ቤቶች ከውድድር ይልቅ አብሮ የመስራት ባህልን በማዳበር የጋራ አላማዎችን ማሳካት እና ሀገር እንዲያድግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ፕረዚደንቷ አጽህኖት በመስጠት ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቶች የጋራ አንድነት ሊፈጥሩ ይገባል ያሉት ፕረዚደንቷ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ምክር ቤቶች ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ ቻምበር በከተማም ሆነ በክልል ደረጃ የሚገኙ የንግድ ምክር ቤቶችን በማቀፍ ተቀራርቦ መስራት እና ስርአት መዘርጋት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
1) Youtube – https: www.youtube.com/@addischamber
7) email: media @addischamber.com
Contact us:
Tel: +251 115 573544
Email: media@addischamber.com
Corporate website: www.addischamber.com
Media website: addischambernews.com