በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ፤ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ስመኘው ተሾመ ፤ አምባሳደሮች፤የንግድ አታሼዎች፤ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ፤ የቦርድ አባላት፤ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ነጋዴዎች፤ጎብኚዎች፤ ስራ ፈጣሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
“ዘላቂነት ያለው ንግድ ተወዳዳሪ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በተከፈተው 27ኛው አዲስ ቻምበር አለምአቀፍ የንግድ ትርኢት በርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ነጋዴዎች ተሳትፈውበታል፡፡
መንግስት እስከዛሬ ንግድ ትርኢቶችን እና ባዛሮችን ከማስተባበር እና ከማገዝ ባለፈ እራሱም እየሰራ መቆየቱን ገልጸው መሰል ዝግጅቶች በምክር ቤቶች እና በግሉ ዘርፍ ተነሳሽነት መዘጋጀታቸው እና መንግስት የማስተባበሩን እና የማገዙን ስራ ብቻ እንዲሰራ ማድረጉ ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን በንግግራቸው ያነሱት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ጃንጥራር አባይ ሲሆኑ አክለውም በከተማዋ መሰል አለም አቀፍ ሁነቶችን ለማስተናገድ ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩ በመሆናቸው መጭው ግዜ የበለጠ ትልቅ እድል ለነጋዴው የሚፈጥር መሆኑን ጠቀመዋል፡፡ አያይዘውም መንግስት አብሮ የመስራት እና የበለጠ የማጠናከር ስራ እንደሚሰራም ጭምር ገልጸዋል፡፡
ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ በመንግስት ጥረት ብቻ የሚመጣ እንዳልሆነ በንግግራቸው ያነሱት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ስመኘው ተሾመ ሲሆኑ ሁሉን አቀፍ እድገት የሚመጣው የግሉ ዘርፍ እና መንግስት በቅንጅት ሲሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በጋራ መስራት እና ንግዱን ማበረታታት የማይተካ ሚና እንዳለው ተጠቁሟል፡፡
ንግድ ዘላቂ የሚሆነው በቴክኖሎጂ ሲታገዝ፣ በአካባቢያዊ ጥበቃ ላይ ሲመሰረት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን ሲችል ብቻ ነው ያሉት ደግሞ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሃመድ ሲሆኑ ንግድ ምክር ቤቱ አባላቶቹ በዓለም አቀፍ ገበያ ብቁ ሆነው እንዲወጡና ለሃገራችን ብልፅግና የላቀ ሚና እንዲጫወቱ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ለተሳታፊ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች ንግድ ትርኢቱ ለወደፊት ትብብር፣ ለዕውቀት ሽግግር እና ለገበያ ማስፋፊያነት እንዲጠቀሙበት መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡27ተኛው አዲስ ቻምበር አለም አቀፍ ንግድ ትርኢት በርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ነጋዴዎች እንዲሁም አዳዲስ ስራ ፈጣሪዎችን ያሳተፈ ሲሆን ለሶስት ተከታታይ ቀናት ለጎብኝዎች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡
27ተኛው አዲስ ቻምበር አለም አቀፍ ንግድ ትርኢት የመዝጊያ ስነ ስርአት እና በንግድ ተወዳዳሪነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲምፖዚየም የሚቀርብበት መሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
