የግሉ ዘርፍ ጥምረት በኑሮ ውድነት ላይ በሚል መሪ ቃል ለሁለት ወራት የሚተገበር መርሐ ግብር መንደፉን የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት አስታወቀ

ም/ቤቱ የተለያዩ ዘርፎችን በመለየት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመወያየት ምክረ ሀሳቦችን ለመንግስት ሲያቀርብ እንደነበር ተገልጿል ።
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ዋና ጸሀፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም እንደተናገሩት በአሁኑ ሰአት አንገብጋቢ ችግር በሆነው የኑሮ ውድነት ዙሪያ ም/ቤቱ የግሉን ዘርፍ በማስተባበር የሚተገበር መርሐ ግብር ነድፏል።
ሶስት መሠረታዊ ተግባራትን አቅፏል የተባለው እና የግሉ ዘርፍ ጥምረት በኑሮ ውድነት ላይ በሚል መሪ ቃል የሚተገበረው መርሐ ግብር በቀጣዮቹ ሀምሌ እና ነሐሴ ወራት የሚከናወን ነው ተብሏል ።
ዋና ጸሀፊው አቶ ሺበሺ እንደገለጹት የመጀመሪያው ተግባር 180 የሚሆኑ የንግድ ም/ቤቱ አባል የሆኑ የምግብ አምራች ኩባንያዎች በአነስተኛ ዋጋ ለህብረተሰቡ ምርት እንዲያቀርቡ ማድረግ ነው።
ሁለተኛው እነዚህ ኩባንያዎች በስራቸው ለሚገኙ ሰራተኞች መሠረታዊ ፍጆታዎችን በድጎማ እና በረጅም ጊዜ በሚከፈል ክፍያ እንዲያቀርቡ የሚል ሲሆን ሶስተኛው በጎዳና ላይ በልመና ላይ ለተሰማሩ ወገኖች የበሰለ ምግብ ማቅረብ መሆናቸውን ገልጸዋል ።
መርሐ ግብሩን ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ እና ከኤግዚቢሽንና ገበያ ልማት ማዕከል ጋር በመተባበር እንደሚከውነው ተነግሯል ።
– በቴሌግራም :- https://bit.ly/3jHql5q
– በፌስቡክ ፡- https://bit.ly/3jIjJ6M
– በትዊተር ፡- https://bit.ly/37MJGzf
– በዌብሳይት :- https://bit.ly/3KOpzz8
ይቀላቀሉና ቤተሰብ ይሁኑን እናመሰግናለን ።